ሰነፉ ልጅ
በከበደ ጋልሻ የተተረከ
በአንድ ወቅት ልጆች የነበሩት ሰው ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ከልጆቹ አንዱ የሚኖርበትን ቤት እንዲሰራለት ይነግረዋል፡፡ ልጁም በመንገዱ ላይ አንዲት አይጥ ያገኝና አይጧም “ና እባክህ እያወራንና ተረት እየተናገርን እንጨዋወት፡፡” አለችው፡፡
ልጁ ግን “አባቴ ቤት እንድስራ አዞኛል፡፡” ቢላትም አይጧ ችግር የለውም ከተቀላለድን በኋላ ትሄዳለህ፡፡” አለችው፡፡ አይጧም ጥሩ ጥሩ ተረቶችን እየነገረችው አዝናናችው፡፡ አይጧ ጨዋታ አዋቂና ተረቶች የማያልቁባት ስለነበረች ልጁ በተመስጦ ሲያዳምጣት ውሎ ምንም ሳይሰራ ቀኑ መሽቶ ወደቤቱ ተመለሰ፡፡
አባትየውም “ቤቱን መስራት ጀመርክ?” ብሎ ሲጠይቀው “አይ! አንዲት አይጥ በመንገዴ ላይ አግኝቼ እሷ ተረት ስታወራኝ ስለመሸ ተመልሼ መጣሁ፡፡ ስራውን ነገ እጀምራለሁ፡፡” አለው፡፡
በሚቀጥለውም አይጧን እንደገና አግኝቷት እንደተለመደው ቀኑ በዋዛ ፈዛዛ አለፈ፡፡
ልጁም ወደቤቱ በተመለሰ ጊዜ ዛሬም ስራውን እንዳልጀመረ ለአባቱ ሲነግረው አባቱ በጣም ተናዶ በሶስተኛው ቀን እንዲሰራ ነገረው፡፡
በሶስተኛውም ቀን አልጀመረም፡፡ በአራተኛውም ቀን ይኸው ተደገመ፡፡ በዚህ ጊዜ አባትየው ሌሎቹን ልጆቹን ጠርቶ “ወንድማችሁ ለእናንተ መጥፎ ምሳሌ ነው፡፡ እርሱ ሰነፍ ነውና እናንተም እንደሱ ሰነፍ እንዳትሆኑ፡፡” አላቸው፡፡
ሰነፉም ልጅ አባቱን ስለፈራው ከቤት ጠፍቶ ከአይጧ ጋር ይኖር ጀመር፡፡
አባትየውመም ሌሎቹን ልጆቹን “ወንድማችሁ ሁልጊዜ ሲያወራና ሲጫወት ጊዜውን በከንቱ ያሳልፋል፡፡ አሁን ደግሞ ጠፍቶ ከአይጧ ጋር እየኖረ ስለሆነ ስንፍናን እንዳያስተምሯችሁ ወደ እርሱ አትሂዱ፡፡” ብሎ መከራቸው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|