ብልጣ ብልጧ ፍልፈል
በኦይሻ ቱሽክሎ የተተረከ
አንበሳ፣ ጅብና ፍልፈል አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ሆኖም አንበሳው በጣም ያሰቃያቸው ስለነበረ ፍልፈሏ አንበሳውን የምታጠቃበትን ብልሃት አዘጋጀች፡፡ ፍልፈሏ የአንበሳው የአጎት ልጅ ብትሆንም ልታጠቃውና ልትበቀለው ወሰነች፡፡
ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን አንበሳው ፍልፈሏና ጅቡ አንድ ምርጥ በሬ አምጥተው እንዲያርዱለት አዟቸው ይህንንም አደረጉ፡፡ በሬውንም ካረዱ በኋላ ጅቡ ፍልፈሏን “አንቺ ሄደሽ አጎትሽን ስታጎርሺው እኔ ሄጄ ከብቶቹን እጠብቃለሁ፡፡” ብሏት ሄደ፡፡
በዚህ ጊዜ ፍልፈሏ አንድ ትልቅ ክብ ድንጋይ ፈልጋ እሳት ውስጥ በመክተት በጣም እንዲግል ካደረገች በኋላ በበሬ ስጋ ጠቅልላ አዘጋጀች፡፡ አንበሳውም ተኝቶ ነበርና “አጎቴ ሆይ፣ እባክህ ንቃ፣ አጎቴ ጥሩ ምግብ አዘጋጅቼልሃለሁ፡፡” ስትለው አንበሳው ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ ፍልፈሏም “በል አፍህን ክፈት፡፡” ብላው አፉን ሲከፍት በስጋ የተጠቀለለውን በጣም የጋለ ድንጋይ አፉ ውስጥ ቀርቅራበት ገደለችው፡፡
ከዚያም ከወለሉ ላይ ካስተኛችው በኋላ ቀጥ አድርጋ በማስተካከል ያንቀላፋ እንዲመስል አደረገችው፡፡
ጅቡም ወደቤት በመጣ ጊዜ “የት ነበርክ? ጌታህ ፈልጎ ስላጣህ እጅግ በጣም ተናዶብሃልና ሊቀጣህ ነው፡፡” አለችው፡፡
ጅቡም አንበሳው ይጎዳኛል ብሎ ስለፈራ ወደከብቶቹ ተመልሶ ሔደ፡፡
ፍልፈሏም አንበሳውን በህይወት ያለ በማስመሰል ጅቡን “ተመልከት! የምትሰራውን ነገር ሁሉ ያያልና ያዘዘህን ነገር ሁሉ ካልፈፀምክ ክፉኛ ይቀጣሃል፡፡ ስለዚህ ትእዛዙን በመከተል እንደወትሮው አርፈህ ከብቶቹን ጠብቅ፡፡ አንበሳው በአንድ አይኑ እየተከታተለህ ነው፡፡” ብላ አስፈራራችው፡፡
ጅቡ በጣም ፈሪ ነበር፡፡
ታዲያ በዚህ ጊዜ ፍልፈሏ የታረደውን በሬ እየበላች አጥንቶቹን በሙሉ ለጅቡ ሰጠችው፡፡
ቀጥላም “አጎቴ ከቤተሰብህ ጋር ጥሩ ግንኙነት መመስረት ይፈልጋል፡፡” ሊጋብዛቸውም ስለሚፈልግ ዘመዶችህን በሙሉ ጥራቸው፡፡” ብላ ለጅቡ ነገረችው፡፡ ጅቡም አንድ ደርዘን የሚሆኑ ጓደኞቹን ወደ ድግሱ ይዟቸው መጣ፡፡ ፍልፈሏም የጅቡን ጓደኞች እንዲቀመጡ ከነገረቻቸው በኋላ አጥንቶች ሰጥታቸው እንዲበሉ ጋበዘቻቸው፡፡
ከዚያም አንበሳውን የምታናግር በመምሰል “አጎቴ ሆይ! በእነዚህ ጅቦች ለምን ትናደዳለህ? ጅቦች ሆይ! አጎቴ ሊያጠቃችሁ እየተዘጋጀ ነውና ተጠንቀቁ፡፡” አለቻቸው፡፡
ወዲያውም የአንበሳውን ቆዳ እንደከበሮ ስትነርተው ጅቦቹ ይህንን ሰምተው አንድ ጊዜ በርግገው በድንጋጤ አካባቢውን ጥለው ጠፉ፡፡ በዚህ ዓይነት ፍልፈሏ ጅቦቹን በሙሉ ከአካባቢው እንዲጠፉና ወደዚያም ቦታ ዳግም እንዳይመለሱ በማድረግ ባለ ድል ሆነች፡፡ ሁሉንም ላሞችና ከብቶችም ለራሷ ወስዳ ሃብታም ሆነች፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|