ፈሪው ሰውና ሚስቱ
በወርቁ ወልደማሪያም የተተረከ
አንድ ፈሪ ባልና ተንኮለኛ ሚስቱ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ሚስቱ ውሽማ ነበራትና ውሽማዋ ወደቤቷ እንዲመጣ ስለፈለገች አንድ ዘዴ ቀየሰች፡፡
ባሏንም “ሽፍቶች ወደዚህ መንደር መጥተው ሰው እየገደሉ ነው፡፡” አለችው፡፡
“የምን ሽፍቶች?”
በዚህ ጊዜ ውሽማዋ መጥቶ “በሩን ክፈቺ!” እያለ በሩን ይደበድብ ጀመር፡፡
ሚስትየውም “ይኸው! ሽፍታው መጣ! በል ተደበቅ!” ስትለው ባልየው ወደጓዳ ገብቶ ተደበቀ፡፡ ውሽማውም ገብቶ “ይህ ቤት ወንድ፣ ወንድ ይሸታል፡፡ እዚህ ቤት ውስጥ ወንድ አለ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
ሚስትየውም “ማንም ወንድ የለም፡፡ ብቻዬን ነኝ፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ምግብ አቅርባ አብረው ከበሉ በኋላ ሽፍታው “ለእግሬ ውሃ አምጥተሸ እጠቢኝ!” ብሎ አዘዛት፡፡
እርሷም የተባለችውን አደረገች፡፡
ከዚያም “አልጋ አዘጋጂልኝና መጥተሸ አብረን እንተኛ!” ብሎ አዘዛት ሚስትየውም “እሺ” ብላ አብረው ተኙ፡፡
እሷም አውቃ ትዕዛዝ እየተቀበለች በማስመሰል ከቆየች በኋላ እኩለ ሌሊት ሲሆን ባልየው ከተደበቀበት ቦታ ማንኮሻኮሽ ይጀምራል፡፡
በዚህ ጊዜ ውሽማው “እዚህ ልታስገድይኝ ነው እንዴ? እዚህ ቤት ወንድ አለ?” ብሎ ሲጮህባት “ኧረ ጌታዬ የለም፡፡ እኔ በዚህ ጎጆ ውስጥ ብቻዬን ነው የምኖረው፡፡ ጥጃዋ ናት ከጓዳ የምታንኮሻኩሸው፡፡” አለችው፡፡
ባልየውም ልክ እንደ ጥጃ “ሙ-----!ሙ-----!” እያለ መጮህ ጀመረ፡፡
ውሽማውም ባልየውን በማሞኘቱ ተደሰተ፡፡ በማግስቱ ጠዋት ተነስቶ ጥሩ ቁርስ በቅቤ (ልክ ፍቅረኞች እንደሚያደርጉት) ከበላ በኋላ ተነስቶ ሄደ፡፡
ሚስትየውም ሽፍታው ከሄደ በኋላ “ያንን ድምፅ ለምንድነው ያሰማኸው? ሊገድለን ይችል ነበር እኮ!” አለችው፡፡ እሱም “አሃ! እኔ ያንቺ ባል! አውቄ እኮ ነው እንደ ጥጃ የሆንኩት፡፡ ታዲያ ይህ ምን ችግር አለው? ለአንቺ ስል እኮ ነው ይህን ያደረኩት፡፡” (እውነቱን ቢያውቀውም እንዳልገባው ሆኖ አሳለፈ፡፡)
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|