ሃዘን ያስረጃል
በወርቁ ዓለሙ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንዲት እርጉዝ ውሻ የነበረችው ሰው ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ሰውየው ከቤቱ ሲወጣ ውሻዋ ተኝታ ነበርና በአጠገቧ ሲያልፍ ከፅንሱ ውስጥ ድምፅ ስለሰማ በጣም ተገርሞ “ፅንስ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ድምፅ ሊያሰማ ይችላል? ተዓምር ነው! አንድ የታወቀ ፈላስፋ አለና ወደእርሱ ዘንድ ሄጄ ስለዚህ ተዓምር መጠየቅ አለብኝ፡፡” ብሎ አሰበ፡፡ ወደዚያም ሄዶ ከአንዲት መንደር ሲደርስ አንድ በጣም ያረጀና በእጆቹም ጭምር መሬቱን እስኪነካ ድረስ የጎበጠ ሽማግሌ አገኘ፡፡
ሽማግሌውንም “ፈላስፋው ሰው አንተ ነህ? አንድ ችግር ላማክርህ ነው የመጣሁት፡፡ አንድ ያልተለመደ ነገር አጋጠመኝ፡፡” አለው፡፡
“አይደለሁም፡፡ እኔ ወጣት ሰው ነኝ፡፡ አባቴ መሬቱን እያረሰ ይገመድለዋል፡፡ ወደ አባቴ ዘንድ መሄድ ትችላለህ፡፡ አባቴ የሚኖረው ከአንድ ስፍራ ነው፡፡ እንቆቅልሹንም እሱ ይፈታልሃል፡፡ ሄደህ አማክረው፡፡”
ሰውየውም “እንዴት ወጣት ነኝ ትላለህ? ቢያንስ አንድ መቶ አመት የሞላህ ነው የምትመስለው፡፡ እሱ አባትህ ከሆነ እድሜው ከመቶ ዓመት በላይ መሆን አለበት፡፡” ብሎት ሄደ፡፡
ከዚያም አንድ ጎልማሳ ሰው አገኘ፡፡
ሰውየውንም “አንተ ነህ ችግሮችን የምትፈታው ፈላስፋ? ወደ አንድ በጣም ያረጀ ሰው ዘንድ ሄጄ አንተ አባቱ እንደሆንክ እያሾፈ ነገረኝ፡፡” አለው፡፡
“አላሾፈም እውነቱን ነው፣ እኔ ፈላስፋ አይደለሁም፡፡ ችግርህንም መፍታት አልችልም፡፡ ከዚህ ተራራ ጀርባ ወዳለው መንደር ሄደህ ችግሮችን የሚፈታውን አባቴን ታገኘዋለህ፡፡ ወደርሱ ሂድና ፈረሶችን ሲገራ ታገኘዋለህ፡፡”
ሰውየውም ወደተባለው መንደር ሲሄድ ይበልጥ ተገረመ፡፡ ወደሶስተኛውም ሰው ዘንድ ሲደርስ አንድ ወጣት ፈረሶችን ሲገራና በሙሉ ጥንካሬ ሲጋልባቸው አየ፡፡
“ፈላስፋው አንተ ነህ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
ወጣቱም ሰው “አዎ” አለ፡፡
ሰውየውም “መጀመሪያ ያገኘሁት ሽማግሌ ሰው ያንተ የልጅ ልጅ እንደሆነና ሁለተኛውም ጎልማሳ አራሽ ሰው ልጅህ እንደሆኑ ነገሩኝ፡፡ እንደዚህ ወጣት ሆነህ ሳለህ እንዴት የእነርሱ አባትና አያት ልትሆን ትችላለህ?” አለው፡፡
“አዎ እውነት ነው፡፡ የሚያርሰው ሰው ልጄ ሲሆን ሽማግሌው ሰው ደግሞ የልጅ ልጄ ነው፡፡”
ሰውየውም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለ፡፡
አያትየውም “በል ና አሳይሃለሁ፡፡” ብሎ ቡና ሊጋብዘው ወደ ቤቱ ይዞት ገባ፡፡ ከቤትም እንደደረሱ ሚስቱን “የፈላስፋውን ሰው መቀመጫ አምጪ፡፡” ብሎ አዘዛት፡፡
እርሷም ወንበሩን ስታመጣ ሰውየው “ይኸኛውን ሳይሆን ሌላኛውን አምጪልኝ፡፡” አላት፡፡
ሚስትየውም ያመጣችውን ወንበር መልሳ ወደሌላ ክፍል ከወሰደችው በኋላ ያንኑ ወንበር መልሳ አመጣችው፡፡
ሰውየውም አሁንም “ይህንን ሳይሆን ሌላውን አምጪልኝ፡፡” ሲላት አሁንም ይዛው ሄዳ ያንኑ ወንበር መልሳ አመጣችው፡፡
ከዚያም ወንበሩ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሚስቱ አይብ እንድታመጣለት ነግሯት አመጣችለት፡፡
“የጥቁሯን ላም ዓይብ ሳይሆን የቀዩዋን አምጪልኝ፡፡” አላት፡፡
እርሷም ያንኑ ዓይብ መልሳ አመጣችለት፡፡
እንደገና “የነጯን ላም ዓይብ አምጭልኝ፡፡” ሲላት አሁንም ያንኑ ዓይብ ታመጣለታለች፡፡ ከዚያ በኋላ ምሣ በልተው ሲያበቁ ሰውየው ማስረዳት ጀመረ፡፡
“ወንበሬን ሶስት ጊዜ አምጭልኝ ስላት አመጣችልኝ፡፡ ዓይቡንም ሶስት ጊዜ አምጪልኝ ስላት አመጣች፡፡ ትዕዛዜን ይፈፅማሉ፡፡ ትእዛዜን ስለምትፈፅም ከሚስቴ ጋር በሰላም እኖራለሁ፡፡ ጭቅጭቅም ሆነ ፀብ በመካከላችን የለም፡፡
አሁን ልጄ ከእኔ በላይ ለምን እንዳረጀና የልጅ ልጄም ከዚያ በላይ ለምን በጣም እንዳረጀ ልንገርህ፡፡ ልጄን ሳዘው ሁሉንም ነገር ያመጣልኛል፣ ያልኩትንም ሁሉ ይፈፅማል፡፡ ፈረሴንም “ና” ስለው ይመጣል፡፡ “ቁም” ስለውም ይቆማል፡፡ ሁሉም ትዕዛዜን ይፈፅማል፡፡ የእርሻ በሬዬም ስጠራው ይመጣል፡፡ እርሻዬንም በትክክል አርሳለሁና በአእምሮ ሰላም እኖራለሁ፡፡ ጥሩ ምርት አገኛለሁ፡፡ ላሞቹ እንኳን በራሳቸው ፍላጎት ነው ወተት የሚሰጡት፡፡ ስለዚህ ዓመት አልፎ አመት ሲተካ ሁሉም ነገር በስኬት የተሞላ ነው፡፡
ልጄ ከእኔ በላይ አርጅቷል፡፡ ፈረሱን ሲጠራው ፈረሱ ይሸሻል፤ ሆኖም እንደምንም ይሳፈረዋል፡፡ የእርሻ በሬው ሥራውን መሥራት አይፈልግም፡፡ ሆኖም እንደምንም ይዞ በትግል ያርስበታል፡፡ ሚስቱ ትዕዛዙን አትፈፅምም፡፡ ነገር ግን በጭቅጭቅ ያበሳጫታል፡፡ አንድ ነገር ለማድረግ ሁልጊዜ ትግል ነው፡፡ ምንም ነገር በትግል እንጂ በራስ መተማመን የሚሰራው ነገር የለም፡፡ ነገሮች ሁሉ እንደፈለገው ባይሄዱለትም እንደምንም ያከናውናቸዋል፡፡ ለዚህ ነው እርሱ ከእኔ በላይ ያረጀው፡፡
የልጅ ልጄ ደግሞ ፈረሱን እንኳን ቢይዘው ፈረሱ መጥቶ ይረግጠዋል፡፡ የእርሻውም በሬ ስራውን በሰላም ከመስራት ይልቅ በቀንዱ ይወጋዋል፡፡ ሚስቱም እርሱ በሚፈልግ ጊዜ ምግብና መጠጥ አትሰጠውም፤ በሰላም እንዲተኛም አታደርግም፡፡ ትነዘንዘዋለች፡፡ በአስከፊ የቃላት ናዳ አንጀቱን ስለምታቆስለው እራት ሳይበላ ይተኛል፡፡ በጣም ይሰቃያል፡፡ ቡና እንኳን እንድትሰጠው መጠየቅ ይፈራል፡፡ እሷ ስትፈልግ ብቻ ነው የምትሰጠው፡፡ መጥፎ ተራጋጭ ፈረሱ ሌላ ሰው ረግጦ ያሳስረኛል ብሎ ይሰጋል፡፡ ሚሰቱ ስለምትበሳጭ ጓደኛውን ለቡና ወደቤቱ ለመጋበዝ ይፈራል፡፡ ፈረሱም የሰዎችን እግር ሲሰብር ቅጣት ይከፍላል፡፡ በከፍተኛ ሃዘን ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ ለዚህ ነው የልጅ ልጄም ቢሆን ሽማግሌና ደካማ የሆነው፡፡ ለዚህም ነው ነገሮች የተገላቢጦሽ የሆኑት፡፡ (እናም ለአንተም ጥያቄ መልሱ ይኸው ነው፡፡ ነገሮች ያረጁ ቢሆኑም ወጣት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡)
ስለዚህ ይህ ፅንስ በጣም ብልህ ሲሆን የልጅ ልጆቹ ብልህ ይሆናሉ፡፡ ከአባቱ የተሻለ ብልህ ቡችላ ይወለዳል፡፡ እናትየዋ እያንቀላፋች መጮህ አለባት፡፡ ነገር ግን ፅንሱ በመጮሁ ከአባቱ የተሻለ ብልህ ይሆናል፡፡ (እናትና ቡችላ የህይወት ተምሳሌቶች ናቸው፡፡)
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|