ሞኙ አሽከር
በአያሌው ኃይሌ የተተረከ
በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖርና አንድ በጣም ሞኝ አሽከር የነበረው አገረ ገዢ ነበር፡፡ አሽከሩ በጣም ጅል ከመሆኑ የተነሳ ምንም ነገር ካለትዕዛዝ አይፈፅምም ነበር፡፡ ስራውን የሚሰራው ሁልጊዜ እየተነገረው ነበር፡፡
“ይህን አድርግ፣ ያንን አድርግ” ካልተባለ ምንም አይሰራም፡፡ ካልተነገረው በስተቀር የፈሰሰ ውሃ እንኳን አያቀናም፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አገረ ገዢው በቅሎውን ተሳፍሮ ወደ ፍርድ ቤት እየሄደ ሳለ የኪስ ቦርሳው ሲወድቅ አገረ ገዢው አላየም፤ አሽከሩም ስላልተነገረው አላነሳውም፡፡ በኋላ ታዲያ አገረ ገዢው ኪሱ ሲገባ ቦርሳው እንደጠፋበት አወቀ፡፡
“ምን ዓይነት ክፉ ቀን ነው! ቦርሳዬን ጣልኩት እኮ!” ሲል አሽከርየውም “እኔ እኮ አይቸዋለሁ፡፡ እንደዚህ፣ እንደዚህ ከተባለ ቦታ ነው የወደቀው፡፡” አለው፡፡
አገረ ገዢውም “ታዲያ ገንዘቤን ስጥል እንዴት ዝም አልክ? ቦርሳዬ ውስጥ ገንዘብ ነበረ፡፡ እንዴት አልነገርከኝም?” አለው፡፡
እርሱም “ጌታዬ ሆይ እንዳነሳው እርስዎም ሆኑ ሌላ ሰው ስላልነገረኝ ነው ዝም ያልኩት፡፡” አለ፡፡
በዚህ ጊዜ አገረ ገዢው በጣም ተበሳጭቶ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር ከኪሱ ወይም ከፈረሱ ኮርቻም ሆነ ከከረጢቱ ውስጥ ሲወድቅ ሲያይ ዝም እንዳይል አስጠነቀቀው፡፡ በሌላ ቀንም ጌታው በበቅሎ ሲሄድ አሽከሩ ኋላ ኋላ በእግሩ እየተከተለ ከጌታውም ሆነ ከበቅሎው የሚወድቅ ነገር መከታተል ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ በቅሎዋ የምትጥለውን ፋንድያ እየሰበሰበ በቅሎዋ በእግሯ ከምትበትነው ጭቃ ጋር አድርጎ በከረጢት ይሰበስብ ጀመር፡፡
ፍርድ ቤቱም ጋ በደረሱ ጊዜ ጌታው “ዛሬስ ምንም ነገር መሬት ሲወድቅ አላየህም?” ብሎ ሲጠይቀው አሽከሩም “አዎ ጌታዬ አይቻለሁ!” አለ፡፡
“ደግሞ ምን ወደቀ?” ሲለው በፋንድያና በጭቃ የተሞላውን ከረጢት አሳየው፡፡
በዚህ ጊዜ አገረ ገዢው በጣም ተበሣጭቶ “ይህንን አይደለም መሰብሰብ የነበረብህ!” ብሎ ጮኸበት፡፡ “ከእንግዲህ ወዲያ የሚከተሉትን ነገሮች ብቻ ነው የምታነሳው፤ቦርሳዬን፣ገንዘቤን፣ባርኔጣዬን፣አለንጋዬንና ማንኛውንም የፈረሱን እቃ፡፡”
አሽከሩም የተባሉትን ነገሮች በዝርዝር ወረቀት ላይ አሰፈረ፡፡ ጌታውም “ከአሁን በኋላ እነዚህን ነገሮች እንጂ ሌላ ነገር እንዳታነሳ፡፡” ብሎ በድጋሜ አስጠነቀቀው፡፡
እናም በሶስተኛ ጉዟቸው እለት እንደተለመደው አሽከርየው ከጌታው ኋላ ኋላ የፃፈውን ማስታወሻ እያነበበ ይከተላል፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ጭቃና ፋንድያ ወረቀቱ ላይ ስላልተፃፉ አላነሳቸውም፡፡ “ጌታዬ እነዚህን ነገሮች እንዳነሳ በፍፁም አላዘዘኝም፡፡” እያለ አሰበ፡፡
በአራተኛውም ቀን ይህንኑ አደረገ፡፡ በወረቀቱ ላይ ያለውን ዝርዝር በጥሞና በመከታተል ላይ ሳለ አንድ አደጋ አጋጠማቸው፡፡ በቅሎዋ በድንገት ተደናቅፋ ስትወድቅ ጌታውም ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ክፉኛ ተጎዳ፡፡
“ና! እባክህ አድነኝ! ከጉድጓዱ ውስጥ አውጣኝ!” እያለ ቢጮህም አሽከሩ “ጌታዬ ሆይ እዚህ ላይ አልተፃፈምና አልነካዎትም፡፡” ብሎ ጉዞውን ቀጠለ ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|