ሞኙ ባልና ብልኋ ሚስት
በአያሌው ሃይሌ የተተረከ
የመክፈቻ ሃረግ
ቶቾ ቶቾ ታኖሬት
አንድሬሸሮ ከፌላ
ጋህሴ ቡቱና ኬላ
ተረት ተረት
(እንሳቅ፣ አዲሱም ልብሳችሁ ይመቻችሁ፡፡)
በአንድ ወቅት በአንዲት መንደር የሚኖሩ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ (በባህላችን እንደተለመደው) ባልየው በጣም ሞኝ ሲሆን ሚስቱ ግን ጎበዝ ነበረች፡፡ እናም በየሳምንቱ ሚስትየው ወደ ገበያ ሄዳ ለቤታቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ስትገዛ ባልየው ደግሞ ልጆቹንና የቤት እንስሳቱን እንዲሁም የአትክልት ስፍራውን ሲንከባከብ ይውላል፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ሚስትየው አንድ መልከ መልካም ወጣት ትተዋወቅና ፍቅረኞች ሆነው በየሳምነቱ ይገናኙ ጀመር፡፡ እሷም ወጣቱን ልጅ በጣም ስላፈቀረችውና ጥልቅ ስሜት ውስጥ ስለገባች ሁልጊዜ ልታገኘውና አብራው ረጅም ጊዜ ልታሳልፍ ፈልጋ በየቀኑ እቅድ በማውጣት ልታገኘው የምትችልበትን መላ ትፈልግ ጀመር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ፍቅረኛዋን እንዲህ አለችው፣ “በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ እያገኘሁህ በመሆኑና አንተ ግን በጣም ስለምትናፍቀኝ በዚህ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ይህ ብቻ በቂ ስላልሆነ ለምን አንድ ቀን አብረን አናድርም?”
እርሱም “ይህማ የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ በርግጥ በጣም እወድሻለሁ፡፡ ነገር ግን አንቺ ትዳር ስላለሽ ይህንን ማድረግ አንችልም፡፡” አላት፡፡
እርሷም “ለዚህም ቢሆን ዘዴ አበጅቻለሁ፡፡ አንተ ጺምህን ትላጭና የሴት ቀሚስ ለብሰህ ሻሽ ካሰርክ እኔ ደግሞ እህቴን ከሃያ አመታት በኋላ አገኘኋት ብዬ ለባሌ አስተዋውቅሃለሁ፡፡ ከዚያም አንተ ሌላኛው ክፍል ውስጥ ስትተኛ እኔም ለብዙ ጊዜ ካላገኘኋት እህቴ ጋር ነው የምተኛው ብዬው ካንተ ጋር እተኛለሁ፡፡” አለችው፡፡ ፍቅረኛዋም በዚህ ተስማምቶ አብሯት ወደቤቷ በመሄድ ቀሚሱን በመልበስ ሁሉም ነገር እንደታቀደው ተዘጋጀ፡፡
እቤትም በደረሱ ጊዜ ሴትየዋ ባሏን “አንተን ከማግባቴ ከሃያ አመታት በፊት የተለየኋት እህቴን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ እንደአጋጣሚ ገበያ ውስጥ አገኘኋት፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል፡፡ ከአንተም ጋር ላስተዋውቅህ ይዣት መጥቻለሁ፡፡” አለችው እርሱም ከእንግዳዋ ጋር ተሳስሞ ተዋወቁ፡፡ ከጥቂት ቆይታም በኋላ ሚስቱ እህቷ በጣም አይን አፋር ስለሆነች ቤተሰቡን እስክትላመድ ድረስ ሌላኛው ክፍል ውስጥ እንድትቆይ ከነገረችው በኋላ ባልየውም ጥሩ በግ ገዝቶ ነበርና ሚስቱ “መቼም ከእህቴ በላይ የምወደው ሰው የለምና በጉን እንረድላት አለችው፡፡”
(በባህሉ መሠረት አንዲት ሴት ፍቅረኛዋን መመገብ አለባት፡፡)
በጉም ታርዶ ጠጅናጠጅ ከማር የሚሰራ የአልኮል መጠጥ ሲሆን ጠላ ደግሞ ባህላዊ ቢራ መሰል መጠጥ ነው፡፡ ጠላ መጥቶ ተበልቶ ተጠጥቶ ደስታ ሆነ፡፡ በኋላም ሚስትየው ባሏን “እህቴ በጣም ናፍቃኝ ስለነበረ አብሬያት መተኛት አለብኝ፡፡” አለችው፡፡
ባልየውም “ምንም ችግር የለም፡፡ አብራችሁ ተኙ፡፡ እኔ ያንቺን ደስታ ነው የምፈልገው፡፡” አላት፡፡
በዚህም ሁኔታ በየቀኑ አብረው እየተኙ ለአንድ ሳምንት ያህል ፍቅራቸውን ሲጋሩ ከረሙ፡፡ ከሳምንት በኋላም ሚስትየው የተለመደ የገበያ ግዢዋን ለማከናወን ወደ ገበያ ሄደች በዚህ ጊዜ ባልየው አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለት፡፡ “ሚስቴ እህቴ ናፍቃኛለች ብላ ለሰባት ቀናት አብራት ስታድር ከረመች፡፡ ስለዚህ ለምን እኔም አብሬያት አልተኛም?” ብሎ በማሰብ ወደ ክፍሏ ገብቶ የድብቅ ፍቅረኛዋን ያነጋግረው ጀመር፡፡ አቅፎ ሊስመው ሲሞክርም ፍቅረኛው ከመሳም እየሸሸ ሚስጥሩም እንዳይታወቅበት ለማድረግ ሞከረ፡፡ ባልየው ግን በጥረቱ ቀጥሎበት የፍቅረኛውን ሰውነት ሲነካው ‹እህት› ተብዬዋ ሰውነቷ እንደወንድ ጡንቻ እንዳለው ደረሰበት፡፡ ባልየው ፍቅረኛዋን ሊይዘው ሲሞክር ፍቅረኛው ደግሞ ለማምለጥ ሲሞክር ትግል ተጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ፍቅረኛው ባልየው ወንድ መሆኑን እንደደረሰበት ስለተረዳ ወጣትና ጠንካራም በመሆኑ ባልየውን ገፍትሮ ጥሎት አመለጠ፡፡
ባልየውም ለራሱ “እንግዲህ ሚስቴ ‹እህቴ› ብላ ወንድ ይዛብኝ መጣች፡፡ ስለዚህ እዚህ ቤት አላስገባትም፡፡ እደበድባታለሁ፡፡” ብሎ አሰበ፡፡ ዱላም አዘጋጅቶ ሊደበድባት ይጠባበቅ ጀመር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ያመለጠው ፍቅረኛ ሚስትየው ከገበያ ስትመለስ ሲያገኛት እርሷም በድንጋጤ “እዚህ ምን ትሰራለህ? ምን ሆንክ? እዚህ ለምን መጣህ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“ምን እባክሽ! እቅድሽ አልሰራም፡፡ ባልሽ እኔ ወንድ እንደሆንኩ አውቋል፡፡ ገፍትሬ ጥዬው ነው ያመለጥኩት፡፡ አሁን ወደቤት ባትመለሺ ነው የሚሻልሽ፡፡ እንደሚደበድብሽ እርግጠኛ ነኝ፡፡” አላት፡፡
እሷም ለአንድ አፍታ አሰብ አድርጋ “ወደቤት መግባት እችላለሁ፡፡ ችግር የለም፡፡ እርሱን የማታልልበት ሌላ ዘዴ አለኝ፡፡” አለች፡፡
“እርሱ ግን ይገድልሻል!”
“አይገድለኝም፡፡ አንተም እንደበፊቱ በየሳምንቱ ገበያው ቦታ ታገኘኛለህ፡፡”
ከዚያም ወደቤቷ ስትቃረብ ባሏን “ወይኔ ውድ ባሌ፣ ወይኔ ባሌ፣እባክህ መጥተህ አድነኝ፡፡” እያለች መጮህ ጀመረች፡፡
ባልየውም በጣም በመገረም “ሚስቴ ችግር ላይ ናት፡፡ ምን ነካት?” እያለ ያስብ ጀመር፡፡
ከዚያም “ምን ነካሽ?” ብሎ ጠየቃት፡፡
እርሷም “ልክ እንደ ተዓምር ዛሬ አንድ ነገር ተከሰተ፡፡ ወንዶችን ወደ ሴትነት፣ ሴቶችን ወደ ወንድነት የሚቀይር ነገር አለ፡፡ እናም የተወሰኑ ወንዶች ወደ ሴትነት፣ የተወሰኑ ሴቶች ደግሞ ወደ ወንድነት ተቀይረዋል፡፡ ከገበያ እየሮጥኩ ነው የተመለስኩት፡፡ እያሳደዱኝ ነበር፡፡ ስለዚህ እባክህ ቶሎ መጥተህ ሳይለውጡኝ ውሰደኝና አንተም ከሚስት አልባነት ዳን፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ባልየው “ለዚህ ነው እህትሽ ወደ ወንድነት ተለውጣ እየሮጠች የሄደችው? ወንድ መስላኝ ነበር፡፡ ለካስ ተሳስቻለሁ፡፡” አለ፡፡
እርሷም “አዎ! ከመለወጥ አምልጬ የመጣሁት እኔ ብቻ ነኝ፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ባልየው ሚስቱን በሰላም ወደ ቤቱ ይዞ ገብቶ የባልና ሚስት ኑሯቸውን ቀጠሉ፡፡
መጨረሻ
የተረቱ አድማጮች እንዲህ ይላሉ
ቶቹኬ፣ ቶቹኬ፣ ጌኔቢቴ
(እግዚአብሔር እድሜ ይስጥህና ብዙ ተረቶች እንድትነግረን ያብቃህ)
ተራኪውም እንዲህ ይላል፤
ኢቶ ካሾ ጌንጃቤ
(እናንተም ተጨማሪ ተረቶችን ለመስማት ያብቃችሁ፡፡)
ወደሚቀጥለው > |
---|