ብልህነት ይነግሳል
በወርቁ ዓለሙ የተተረከ
በድሮ ጊዜ አሁንም ድረስ ያሉ ማቶ የሚባሉ የጎሳ አባላት ነበሩ፡፡ የማቶ ጎሳ አባላት በጣም ብልህና ጎበዝ ስለነበሩ ሚንጆ እየተባሉ የሚጠሩትን የካፋ ነገስታት በኋላ እስከተባረሩበት ጊዜ ያማክሯቸው ነበር፡፡ ሆኖም ማቶዎች ከንጉሱ ጋር በእውቀት ይፎካከሩ ስለነበረ ንጉሱ ሁሉም የጎሳው አባላት በስቅላትና በሞት አልቀው ከማህበረሰቡ እንዲወገዱ አዘዘ፡፡ እናም አብዛኛዎቹ ማቶዎች ሲሰቀሉ የቀሩት ተሰደዱ፡፡ ታዲያ አንድ ትንሽ የማቶ ጎሳ አባል የነበረ ልጅ ተደብቆ ማኖ ከተባለው ጎሳ (በቆዳ ፋቂነት የሚተዳደርና በህብረተሰቡ ተገልሎና ተጠልቶ የሚኖር ሌላ ጎሳ) አባላት ጋር አደገ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ንጉሱ እጅግ በጣም ትልቅና ከጎረቤት ነገስታት ቤተ መንግስቶች በላይ ያማረ ቤተመንግስት ለመገንባት አስቦ ጠባቂዎቹን በጣም ረጅምና ሰማይ የሚነካ ቋሚ እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ማንም ሰው የንጉሱን ትዕዛዝ እምቢ ማለት አይችልምና ጠባቂዎቹም ይህንኑ አይነት ቋሚ ፍለጋ ተሰማሩ፡፡ ቋሚውን ካላመጡ የሚከተላቸው ስቅላት ነውና ሩቅና ሰፊ ግዛትን ያካለለ ፍለጋ አደረጉ፡፡
ታዲያ ይህንኑ ሰማይ የሚነካ ቋሚ ፍለጋ ለአስር አመታት ሲንከራተቱ ጥፎሮቻቸውንም ሆነ ፀጉራቸውን መቁረጫ ምንም ጊዜ ስላላገኙ ጥፍሮቻቸው እጅግ በጣም ረዛዝመውና ፀጉራቸውም ጀርባቸውን እንደልብስ እስኪሸነፍው ድረስ ተንዠርጎ ነበር፡፡
ቋሚውንም እስኪያገኙ ድረስ ወደ ንጉሱ መመለስም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ማየት አይችሉም ነበር፡፡
በጫካ ውስጥ መኖር ስለሰለቻቸውና ቋሚውንም ለመፈለግ ከንጉሱ መደበቅ ስላማረራቸው ወደ አንድ መንደር ለመሄድ ወስነው ወደ አንዲት መንደር በመሄድ የመንደሩን ልጆች ሲያነጋግሩ የማቶውን ልጅ አገኙት፡፡
ይህ ልጅ ከማኖዎች ጋር ያደገ ሲሆን ማኖዎቹ የሰዎቹን ረጃጅም ጥፍሮችና ፀጉር ሲያዩ “እነዚህ ምን አይነት ፍጡራን ናቸው?” እያሉ ሲሸሿቸው የማቶው ልጅ ግን ቀርቧቸው ምን እንደሚፈልጉ ጠየቃቸው፡፡
እነርሱም “ለምንድነው የምትጠይቀን? ምንስ ታደርግልናለህ?” አሉት፡፡ እርሱም “ግዴላችሁም ንገሩኝ!” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሱ አምጡ ብሏቸው ስላዘዛቸው ቋሚና እነርሱም ይህንኑ በመፈለግ ንጉሱን ፍራቻ በጫካ ውስጥ የጫካ ፍሬዎችንና የዱር እንስሳትን እየተመገቡ መቆየታቸውን ነገሩት፡፡ በመጨረሻም “ያለን ብቸኛ እድል መሰቀል ብቻ ነው፡፡” አሉት፡፡
ልጁም “እኛ ጫካ ውስጥ እንድትደበቁና ከዚህ እዚያ ስትንከራተቱ እንድትኖሩ ያደረገቻችሁ ይህቺ ትንሽ ችግር ናት?” አላቸው፡፡
እነርሱም “አዎ” አሉት፡፡
የማቶውም ልጅ “ይህንን ችግር እኔ እፈታዋለሁ፡፡” አለ፡፡
ሆኖም እነርሱ ስላላመኑት “በፍፁም አናምንህም አሉት፡፡” በርግጥም እውነት አልመሰላቸውም ነበር፡፡
“ይህንን ችግር ከፈታህልን የፈለከውን ሁሉ እናደርግልሃለን፡፡” አሉት፡፡ ልጁም “እኔ ካልረዳኋችሁ የካፋ ንጉስ ያሰቅላችኋልና ማድረግ ያለባችሁን ነገር እኔ እነግራችኋለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ እንደነገርኳችሁ እንዳትናገሩ፡፡ በሉ አሁን ከበሮ ፈልጋችሁ የደስታ ዘፈን የሆነውን ‘ዩቦ’ (የካፋ ቃል) እየዘፈናችሁ በቀጥታ ወደ ንጉሱ በመሄድ ከቤተመንግስቱ በደረሳችሁ ጊዜ ‘አንተ የተወደድክ ንጉስ ሆይ! ለሺህ አመታት ንገስ፡፡ የፈለከውንም ቋሚ አግኝተናል፡፡ ነገር ግን ርዝመቱ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ስለማነውቅና ሰማይም በጣም ሩቅ ስለሆነ ቋሚውን የምንለካበት ዘንግ ጃንሆይ ትሰጠን ዘንድ መጥተናል’ በሉት፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም ከበሮውን እየመቱና ዩቦን እየዘፈኑ ወደ ቤተመንግስቱ መጡ፡፡ ንጉሱም ባያቸው ጊዜ እየሳቀ “ሲያስመስሉ ነው! ሰማይን የሚነካ ቋሚ እንዴት ሊያገኙ ይችላሉ? ምን እንደሚሉ እሰማለሁ፡፡ ቋሚውን ያገኙ ይመስል እየተደሰቱ ነው፡፡” ብሎ ይጠብቃቸው ጀመር፡፡ እነርሱም “ንጉስ ሆይ ለሺህ ዓመታት ንገሰ፡፡ ቋሚውንም አግኝተናል፡፡” አሉ፡፡
ንጉሱም “ታዲያ ለምን አላመጣችሁትም?” አላቸው፡፡
እነርሱም “የቋሚውን ርዝመት የምንለካበት ዘንግ ስለሌለን እባክህ ዘንጉን ስጠንና ቋሚውን እናምጣ፡፡” አሉት፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሱ ነገሩ ገብቶት “ከማቶኒ ጎሳ አንድ የቀረ አባል አለ ማለት ነው፡፡ ይህ አጭበርባሪ ማቶኒ ነው ይህንን በሉ ያላችሁ፡፡” ሲላቸው እነርሱም “ማንም አልነገረንም፡፡” አሉ፡፡
መናገሩን እምቢ ቢሉም ባይናገሩ እንደሚሰቅላቸው ስለሚያውቁ በመጨረሻ አንድ ትንሽ ልጅ እንደነገራቸው አመኑ፡፡ ንጉሱም ወታደሮቹ ሄደው ልጁን እንዲያመጡ ካዘዛቸው በኋላ ልጁም ማቶኒ እንደሆነና ከቆዳ ፋቂዎቹ ጋር እንደሚኖር ተናገረ፡፡ “ስቅላትንና ሞትን ለማምለጥ ስል ከማኖዎቹ ዘንድ አደኩ፡፡” አለ፡፡ ይህንን በሰማ ጊዜ ንጉሱ “ይህንን ችግር መፍታት ከቻልክ ሌሎቹንም ችግሮቼን መፍታት ትችላለህና ብልህ ነህ፡፡” ብሎ አደነቀው፡፡
ቀጥሎም “ከዚህ በኋላ ማንም አይሰቅልህም ከአሁን ወዲያ ያንተ ጎሳ አይሰቀልም፣ አይገደልምም፡፡ ከማቶ ጎሳዎች ጋር የእኔ አማካሪ ትሆናለህ፡፡” ብሎ አወጀ፡፡ በስደት ላሉትም ምህረትና ያለመገደል መብት እንዲህ ብሎ ሰጣቸው፤
“የአንተ ጎሳ አባላት በሙሉ ተመልሰው ከእኔ ጋር በሰላም ይኖራሉ፡፡ ከአሁን በኋላ ከቤተ መንግስቴ ርቃችሁ አትኖሩም፡፡ በስደትም ላይ ያሉት ወደ ሃገራቸው ይመለሱ፡፡”
እናም ከዚያች እለት አንስቶ የማቶ ጎሳ የከፋን ነገስታት እያማከሩ በሰላም መኖር ጀመሩ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|