ተንባዩና ቀበሮው
በዘሪቱ ከበደ
በአንድ ወቅት አንድ የወደፊቱን መናገር የሚችል ሽማግሌ አማካሪ የነበረው ንጉስ ነበር፡፡ ታዲያ አዛውንቱ ሰው ሲሞት ንጉሱ ወደ ልጁ ልኮበት ስለ ወደፊቱ እንዲተነብይ ጠየቀው፡፡ ልጁ ግን ምንም ማድረግ ስለማይችል በጣም አዘነ፡፡
ሆኖም ልጁ ወደ ንጉሱ ቤተ መንግስት እየሄደ ሳለ አንድ ቀበሮ አገኘ፡፡ ቀበሮውም ልጁን “ሃምሳ በጎች ከሰጠኸኝ ስለወደፊቱ ልነግርህ እችላለሁ፡፡” አለው፡፡
ልጁም በዚህ ከተስማማ በኋላ ቀበሮው “የሚቀጥሉት ጥቂት አመታት የእሳትና የቃጠሎ እንደሚሆኑ ለንጉሱ ንገረው፡፡” አለው፡፡
ልጁም ወደ ንጉሱ ሄዶ ይህነኑ ነገረው፡፡ ነገር ግን ቃል የገባውን በጎች ከማምጣት ይልቅ እሳት ይዞ መጥቶ ቀበሮውን ሊያቃጥለው ሞከረ፡፡
ከሶስት ዓመታት በኋላ ንጉሱ አሁንም ወደ ልጁ መልዕክት ሲልክ ልጁ ቀበሮውን እስኪያገኘው ድረስ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገባው፡፡ ነገር ግን ቀበሮው አሁንም “ሃምሳ በጎች ካመጣህልኝ ስለወደደፊቱ እነግርሃለሁ፡፡” አለው፡፡
ልጁም እንደገና ቃል ገብቶ ቀበሮው የሚቀጥሉት ሶስት አመታት የጦርነት ጊዜ እንደሚሆኑ ነገረው፡፡
በዚህም ጊዜ ለቀበሮው በጎች ከማምጣት ይልቅ ጦር ይዞ መጥቶ ቀበሮውን ሊገድለው ሞከረ፡፡
ከሶስት አመታት በኋላ ንጉሱ አሁንም ወደ ልጁ ሲልክበት ቀበሮው መንገድ ላይ አግኝቶት መጪው ጊዜ የሰላም እንደሚሆን ነገረው፡፡
በዚህ ጊዜ ልጁ ሄዶ ሃምሳ በጎችን ለቀበሮው አምጥቶለት ዘመኑም የሰላም ሆኖ ሰዎቸና እንስሳት እንዲሁም ልጁና ቀበሮው ታርቀው በሰላም አብረው መኖር ጀመሩ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|