ድሃው ሰውና ሃብታሙ ሰው
በዘሪቱ ከበደ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ ድሃና አንድ ሃብታም ሰዎች ነበሩ፡፡ ድሃው ሰው ዝም ብሎ የሚኖርና በልብሶቹ ላይ ካሉት ተባዮች በስተቀር ምንም ነገር ያልነበረው ሰው ነበር፡፡ ሃብታሙ ሰው ግን ጠንካራ ሰራተኛና ቅዳሜና እሁድንም ጭምር እየሰራ ሃብታም የሆነ ሰው ነበር፡፡
ሰዎቹም የድሃውን ሰው ሚስት ባሏ ድሃ ለምን እንደሆነና ሌላው ሰው እንዴት ሃብታም እንደሆነ ሲጠይቋት እሷም “ባሌ እኔ በፈጣሪ የማምን ሰው ነኝ፡፡ በጌታ ስለማምን ሙሉውን ጊዜዬን ወደ ጌታ በመፀለይ ወደርሱ በመቅረብ ነው የማሳልፈው፡፡ ሃብታሙ ሰው ግን ሙሉውን ጊዜ ሃብት ሲያሳድድ ነው የሚሳልፈው፡፡” ብሎኛል ብላ ነገረቻቸው፡፡
ከዚያም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰዎቹ አምላካቸው ውለታ እንዲውልላቸው ፈልገው ወደ ድሃው ሰው በመሄድ እርሱ ወደ አምላክ የቀረበ ሰው በመሆኑና ወደ መንግስተ ሰማይ ለመግባት የሚፈቀድለት በመሆኑ እርሱ እንዲፀልይላቸው ሊጠይቁት ወሰኑ፡፡
በመንገዳቸውም ላይ አንድ አዛውንት አግኝተው አዛውንቱ ወዴት እንደሚሄዱ ሲጠይቋቸው እነርሱም ወደ ድሃው ሰው ዘንድ ሄደው ለአምላክ እንዲፀልይላቸው ሊጠይቁት መሆኑን ነገሩት፡፡
አዛውንቱም ሰው “ድሃው ሰው ከሃብታሙ ሰው የተሻለ ፃዲቅና ለአምላክ የቀረበ መሆኑን እርግጠኛ ናችሁ? ማረጋገጫችሁስ ምንድነው? የልቡን ውስጥ ማየት አትችሉ፡፡ ሆኖም ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ልንገራችሁ፡፡ ድሃው ሰው አንድ ውሻ ሲኖረው ሃብታሙ ሰው አንድ ወንድ ልጅ አለው፡፡ ስለዚህ ሂዱና ሁለቱንም ግደሏቸው፡፡” አሏቸው፡፡
ከዚያም ሰዎቹ ሄደው ውሻውንና ልጁን ገደሏቸው፡፡ ከዚህ በኋላ አዛውንቱ ሰው ጠርተዋቸው “አሁን ወደ ድሃውና ወደ ሃብታሙ ሰው ሄዳችሁ ለሁለቱም ካሳ እንደምትከፍሏቸው ንገሯቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በካሳው ከተስማሙ ውሻውንም ሆነ ልጁን የገደሉትን ሰዎች አይበቀሏቸዉም ማለት ነው፡፡” አሏቸው፡፡
ሃብታሙም ሰው ካሳውን እንደሚቀበልና በማንም ላይ የበቀል እርምጃ እንደማይወስድ ተናገረ፡፡ ልጁንም አምላክ እንደሰጠውና እሱው መልሶ እንደወሰደው ተናገረ፡፡ ድሃው ሰው ግን ምንም አይነት ካሳ እንደማይቀበልና እንዲያውም ውሻውን የገደሉትን ሰዎች እንደሚበቀላቸው ተናገረ፡፡
ስለዚህ ይህ የሚያሳየው ድሃው ሰው ደም የጠማውና ብዙ አረመኔያዊ ሃሳቦችን በልቡ የያዘ ሰው መሆኑን ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለውሻ ምንም ዓይነት ካሳ እንዳይከፈል የኦሮሞ አባቶች ወሰኑ፡፡
የዚህም ታሪክ መልዕክት የሚያሳየው ሃብታም ሰው ፃዲቅ ሊሆን እንደሚችልና ድህነት ሁልጊዜ መልካም መሆን ማለት እንዳልሆነ ነው፡፡
< ወደኋላ |
---|