የአባትየው ምክር
በሞቱ ወዬሣ የተተረከ
በአንድ ወቅት ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስትየው አረገዘች፡፡ ባልየው ግን መሞቻው ተቃርቦ ነበርና ሚስቱን “አዳምጪ፣ የሚወለደው ልጅ ወንድ ከሆነና እኔ ከሞትኩ ሶስት ምክሮች ስጪው፡፡ አንደኛው ምክር ሚስቱን ሰርግ ወዳለበት ቦታ ለአዳር እንዳይሰድ፤ሁለተኛው ምክር ደግሞ እርጉዝ ፈረሱን ለግልቢ እንዳይሰጣትና ሶስተኛውም ምክር በቸገረው ጊዜ በፍፁም ወደ እህቱ ቤት እንዳይሄድ የሚል ነበር፡፡
ይህንንም ካለ በኋላ ሰውየው ሲሞት ሚስቱ በርግጥም ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ልጁም ባደገ ጊዜ እናቱ የአባቱን ምክር መከረችው፡፡ ልጁ ታዲያ አባቱ ለምን እነዚያን ምክርች እንደተወለት ለማወቅ ስለጓጓ አድጎ ካገባ በኋላ ከእለታት አንድ ቀን ሚስቱን ወደ አንድ የሰርግ ድግስ ሄዳ እንድታድር ላካት፡፡ በዚህ ጊዜ ራሱን በመቀየር ወደ ሰርግ ቤቱ ተሰውሮ ሲሄድ ሚስቱን ስትጠጣና ስትጨፍር አገኛት፡፡ እርሱም አብሯት ይጠጣና ይጨፍር ጀመር፡፡ ሆኖም ሚስቱ ማንነቱን አላወቀችም ነበርና አብሯት ለመተኛት ሲጠይቃት እሺ አለችው፡፡ ከዚያም ይዟት ሄዶ አብረው አደሩ፡፡
በንጋታው ጠዋት አሁንም አላወቀችውም ነበር፡፡ እርሱም “አብረን ለማደራችን ምልክት የሚሆነኝ ነገር ስጪኝ” ብሎ ሲጠይቃት አብሯት ያደረው ባሏ መሆኑን ባለማወቅ የአንገቷን ሃብል በጥሳ ሰጠችው፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ አንድ ጓደኛው ፈረሱን ሊዋስ መጣ፡፡ እሱም እርጉዝ ፈረሱን ከሰጠው በኋላ ራሱ በሌላ ወንድ ፈረስ በመሆን በሩቅ ይከታተለው ጀመር፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ጓደኛው ፈረሷን በሃይል ይጋልባት ስለነበረ ፅንሱ ጨነገፈ፡፡ ጓደኛው ግን ፈረሷን ምንም ፋታ ሳይሰጣት ጭንጋፉን ከወረወረ በኋላ አሁንም በተቻለ ፍጥነት ሁሉ ይጋልባት ጀመር፡፡
የፈረሷም ባለቤት ከፈረሱ ወርዶ ማስረጃ ይሆነው ዘንድ ከጭንጋፉ ላይ ትንሽ ቁራጭ ስጋ ይዞ ሄደ፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ አሮጌ ልብስ ለብሶ ወደ እህቱ ቤት በመሄድ “እህቴ ሆይ፣ የአባታችንን ንብረት በሙሉ አጥቼ ድሃ ሆኛለሁ፡፡” አላት፡፡
እሷም “እንደ ለማኝ ውጪ ተቀመጥ፡፡” አለችው፡፡
የእህቱም ባል “ወንድምሽ ነውና ወደ ቤት አስገቢውና የሚለበስ ልብስና ምናልባትም አንዲት ላም ልንሰጠው እንችላለን፡፡” ሲላት እሷም በፍፁም አሻፈረኝ በማለት “ገንዘባችንን በሙሉ ካጠፋው ምንም ጥቅም የለውም፡፡” ብላ ለለማኝ የሚሰጠውን ያህል አንድ እፍኝ ጥሬ ዘግና ሰጠችው፡፡
ሰውየውም ወደ ቤቱ ተመልሶ ትልቅ ድግስ ካዘጋጀ በኋላ ወደ እህቱ መልዕክተኛ ልኮ “የአባታችንን ሃብት መልሼ ስላገኘሁት ሃብታም ሆኛለሁና ነይ፡፡” ብሎ ጠራት፡፡
ወደ ጓደኞቹም መልዕክት ልኮ “ከእኔ ቤት እንድትመገቡ ስለምፈልግ ኑ፡፡” ብሎ ጠራቸው፡፡
ሚስቱም ቤቱ ውስጥ ነበረችና አዛውንቶቹን በሙሉ ሰብስቦ “ለሁላችሁም አንድ ነገር ልነግራችህ እፈልጋለሁ፡፡” አላቸው፡፡
“አባቴ ሲሞት ሶስት ብልህ አባባሎችን ትቶልኝ ነበር የሞተው፡፡ የመጀመሪያው ሚስቴ ሰርግ ቤት ሄዳ አንዳታድር፤ሁለተኛውም እርጉዝ ፈረሴን ለጓደኞቼ እንዳላውስና ሶስተኛው ደግሞ በቸገረኝ ጊዜ እህቴ ቤት እንዳልሄድ ነበር፡፡ የአባቴንም ምክሮች በሙሉ ፈትሼያቸው በእርግጥም ሁሉም እውነት መሆናቸውን አረጋግጫለሁ፡፡ ይህ የሚስቴ የአንገት ሃብል ነው፡፡ ራሴን ቀይሬ በመሄድ አብሬያት ሰርጉ ቤት አድሬአለሁ፡፡ ታዲያ እውነትም እንግዳ ሰው ሆኜ ብሆን ኖሮ ይህ እምነትን ማጉደል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፈረሴ ያስጨነገፈችው ጭንጋፍ እግር ሲሆን ጓደኛዬ ክፉኛ ጋልቧት ነበር፡፡ በመጨረሻም ይህ እህቴ የሰጠችኝ እፍኝ ጥሬ ነው፡፡ ስለዚህ የአባቶቻችንንና የአዛውንቶችን ምክር ሁልጊዜ መቀበል አለብን፡፡” አላቸው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|