መንትዮቹ ወንድማማቾች
በሞቱ ወዬሳ የተተረከ
በአንድ ወቅት አብረው የሚኖሩ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ ሚስትየውም ባረገዘች ጊዜ ጠንካራ ትሆን ዘንድ ብዙ በጎችን እያረደ ያበላት ነበር፡፡
ጊዜው በጣም ሄዶ ዘጠኝ ወር ደረሰ፡፡ ባልየውም ለፈጣሪ እንዲህ እያለ ፀለየ “አምላኬ ሆይ፣ እባክህ ተጨማሪ ምግብ በልታ እስክትጠነክር ድረስ ህፃኑን በማህፀኗ ውስጥ ትንሽ አቆየው፡፡”
እናም አምላክ የሁሉንም ፀሎት ይሰማልና ህፃኑ በእናቱ ማህፀን ውስጥ ቆየ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባልየው ከሚስቱ ጋር መኖሩን ስለቀጠለ ያረገዘችውን ህፃን ሳትወልድ በድጋሚ ሌላ ልጅ አረገዘች፡፡
እናም ከዘጠኝ ወራት በላይ በነፍሰጡርነት ከቆየች በኋላ መንትያ ልጆች ወለደች፡፡ ሆኖም አንደኛው ህፃን ግን በእናቱ ማህፀን ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱ ከሁለተኛው ህፃን በእድሜ በጣም ይበልጥ ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ መንትዮቹ ተወልደው አብረው አደጉ፡፡ ከጊዜ በኋላም እናትየው ስትሞት ልጆቹ ወራሽ የትኛቸው መሆን እንዳለበት መወሰን ነበረባቸው፡፡
ታላቅየውም ልጅ “እኔ ታላቅ ስለሆንኩ ውርሱ የሚገባኝ እኔ ነኝ፡፡” አለ፡፡ ታናሽየው ልጅ ግን “የተወለድነው በአንድ ጊዜ በመሆኑ አንተ ከእኔ በእድሜ አትበልጥም፡፡” አለው፡፡
ከዚያም ወደ አገር ሽማግሌዎች ሄደው ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን ለመዳኘት ተቸገሩ፡፡ ስለዘህ ልጆቹን ወደ አንድ ሃይቅ ወስደው “ይህንን ጉዳይ እኛ መዳኘት አንችልምና ውሳኔውን ለፈጣሪ ነው መተው ያለብን፡፡” አሉ፡፡ በጉዳዩም ላይ አባገዳን ያማከርን ሲሆን መፍትሄውም ሁለታችሁም ወደ ሃይቁ ወለል ወርዳችሁ ያገኛችሁትን ነገር ይዛችሁ ትወጣላችሁ፡፡” አሏቸው፡፡
መንትዮቹም በዚህ ተስማምተው ወደ ሃይቁ ውስጥ ዘለው ገቡ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታናሹ ወንድም ዓሣ ይዞ ሲወጣ ታላቅየው ደግሞ ከለቼ በእጁ ይዞ ወጣ፡፡ የኦሮሞ ብሔር አባላት ከለቼን በዚሁ ሁኔታ እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ እናም በዚህ ምክንያት ነው የብሔሩ የበኩር ልጆች ከታናናሾቹ ይልቅ ከለቼው የሚሰጣቸው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|