ላባ ያበቀለው ሰው
በወርቁ ደበሌ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሁለት ወንድ ልጆች የነበሩት ሰው በሞተ ጊዜ በሶስቱም በረት ውስጥ (ማለትም ላሞቹን በሙሉ) ለመጀመሪያ ልጁ አውርሶ ለሁለተኛው ልጅ ግን አንድ አውራ ዶሮ ብቻ ተናዞለት ሞተ፡፡ በሰውየውም ኑዛዜ መሠረት ለመጀመሪያው ልጅ ሶስቱም በረት ላሞች ሲሰጡት ሁለተኛው ልጅ አንድ አውራ ዶሮ ብቻ ተሰጠው፡፡
ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሃብታሙ ልጅ በጠና ስለታመመ ወደ አንድ መድኃኒት አዋቂ ሰው ዘንድ ሄዶ ከበሽታው ይድን ዘንድ ምን ማድረግ እንዳለበት ጠየቀው፡፡
መድኃኒት አዋቂውም “ልዩ መልክ ያለው አውራ ዶሮ ማረድ አለብህ፡፡” አለው፡፡
ሃብታሙ ልጅም እንደዚያ ያለ ዶሮ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ሲያስብ ቆይቶ የወንድሙ አውራ ዶሮ ትዝ አለው፡፡ ከዚያም ሰዎች ወደ ወንድሙ ሄደው ዶሮውን እንዲያመጡለት ላካቸው፡፡
ወንድምየውም ሰዎቹን “ያለኝ አንድ ንብረት ይህ ዶሮ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ወንድሜ መዳን የሚችለው በዚህ ዶሮ ከሆነ ዶሮውን አጥቼ ወንድሜ ወደ ጤናው ቢመለስ ይሻለኛል፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ሁኔታ ዶሮውን ለሰዎቹ ሰጥቷቸው ሰዎቹም ዶሮውን ወስደው ካረዱት በኋላ ደሙን አፍስሰው ለመጀመሪው ወንድም መገቡት፡፡
ከዚህ በኋላ ወንድምየው ድኖ ወደቤቱ ከተመለሰ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ አስገራሚና ያልተለመደ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ ይኸውም ከበሽታው የዳነው ወንድም ሰውነቱ ላይ ላባ ማብቀል መጀመሩ ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ወንድምየው በጣም ደንግጦ ወደ መድኃኒት አዋቂውና ወደ አገር ሽማግሌዎች ተመልሶ ሄደ፡፡
እነርሱም ይህንን ተመልክተው “ይህ በሌላ ሰው ላይ ክፋት በሚሰራ ሰው ላይ የተጣለ ርግማን ነው፡፡ አንተም ወንድምህ ላይ ክፋት ሰርተሃል፡፡ አባታችሁ ትቶ የሞተውን ከብቶች ብቻ ሳይሆን ለእርሱ የተናዘዘለትን አንድ አውራ ዶሮ እንኳን ሳይቀር በሙሉ ጠራርገህ ወስደሃል፡፡ ስለዚህ ከችግርህ ትላቀቅ ዘንድ ወንድምህ ይቅር ሊልህ ይገባል፡፡ ስለዚህ ይህንን ከለቼ (የኦሮሞ ባህላዊ ቁስ) ወስደህ ለይቅርታ ተምሳሌትነት ለወንድምህ ስትሰጠው እላዩ ላይ ከተፋበት ትድናለህ፡፡” አሉት፡፡
ታናሽየውም ወንድም ስለተፋለት አዛውንቶቹ አንድ በረት ላሞች ሰጡት፡፡
የዚህ ታሪክ መልዕክት የተትረፈረፈ ሃብት ካለህ ለሌሎችም ማሰብ እንዳለብህ ያመለክታል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|