አውራ ዶሮው
በወርቁ ደበሌ የተተረከ
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አውራ ዶሮ አደአ ወደሚባል ቦታ ሄዶ ከብቶችን ዘርፎ እንደሚመጣ ሲናገር ሰዎቹ ሁሉ ስቀውበት “አውራ ዶሮ ደካማ በመሆኑ አንተም ከብቶች መዝረፍ አትችልም፡፡” አሉት፡፡
እሱም ፈገግ በማለት “ደካማ ልሆን እችል ይሆናል ነገር ግን በጣም ብልህ ነኝ፡፡” አላቸው፡፡
ከዚያም ዶሮው የተወሰኑ እንስሳትን አስከትሎ ሄደ፡፡ አንበሳን፣ እርኩይን የተባለውን ትልቅ ወፍ፣እባብና አይጥ ይዞ ሄደ፡፡ ከዚያም አደአ ወደሚባለው ቆላ ወረዳ ሄዱ፡፡ እዚያም ሲደርሱ ብዙ ላሞች ወደ ታሰሩበት ከፍታ ቦታ ላይ ወጡ፡፡
ዶሮውም “አይጥ ሆይ፣ ያንተ ድርሻ ወደ ላሞቹ ሄደህ ላሞቹ የታሰሩበትን ገመድ በሙሉ አኝከህ መበጣጠስ ሲሆን ከዚያም ላሞቹን እየነዳን እንሄዳለን፡፡” አለ፡፡
በዚህ ሁኔታ አይጡ ገመዱን ቀረጣጥፎ በልቶ ሁሉንም ላሞች ለቀቃቸው፡፡ ከዚያም የአንበሳው ተራ በደረሰ ጊዜ አንድ ጊዜ በኃይል ሲያገሳባቸው ላሞቹ ደንብረው ከታሰሩበት ግር ብለው ወጡ፡፡ የከብቶቹም ባለቤቶች ተነስተው ከብቶቻቸውን ተከትለው ሲሮጡ አውራ ዶሮው ለእነርሱም ወጥመድ አዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ ይኸውም እባቡ መንገዳቸው ላይ እንዲተኛ በማድረግ ሁሉንም ሰዎች እንዲነድፋቸው አደረገ፡፡
በዚህ አይነት ከብቶቹን በሙሉ እየነዱ ወደመጡበት ከተማ በመመለስ ላይ እያሉ ዶሮው ወደ እባቡ ሄዶ “አዳምጥ፣ ወደ መንደራችን ስንመለስ ማንኛችንም አንሞገስም፡፡ ሙገሳው በሙሉ የሚሰጠው ለአንበሳው ነው የሚሆነው ምክንያቱም እርሱ በጣም ጠንካራ ስለሆነ ሰዎች ሁሉ ከብቶቹን ዘርፎ የመጣው እሱ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡” አለው፡፡
እባቡም “ታዲያ ምን ባደርግ ይሻላል?” አለ፡፡
ዶሮውም “እንግዲያው አፍንጫው ላይ ብትነድፈው ነገሮች ሁሉ ጥሩ ይሆናሉ፡፡ ስራውን እንደሆን ጨርሷል፡፡” አለው፡፡
ስለዚህ እባቡ ወደ አንበሳው ሄዶ ነድፎ ገደለው፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላም ዶሮው ወደ ትልቁ ወፍ ሄዶ “አዳምጥ፣ እባቡ አንበሳውን ከገደለ ነገ ደግሞ አንተንም፣እኔንም እንዲሁም ሌሎቹንም እንስሳት ይገድላል፡፡ ስለዚህ ለምን እባቡን አትውጠውም?” አለው፡፡
ከዚያም ወፉ ሄዶ እባቡን ዋጠው፡፡
ቀጥሎም ዶሮው ወደ አይጡ በመሄድ “አዳምጥ፣ጭልፊቱ ሃይለኛውን እባብ መግደል ከቻለ በእርግጠኝነት እኛንም መግደሉ አይቀርም፡፡” አለው፡፡
አይጡም በፍራቻ ተውጦ “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለ፡፡ ዶሮውም “እንግዲያው ወፉ ሲተኛ ክንፎቹን ብትቀረጣጥፋቸው ተከትሎን መብረር አይችልም፡፡” ብሎ መከረው፡፡
አይጡም ሄዶ የወፉን ክንፎች ቀረጣጠፋቸው፡፡
ከዚህ በኋላ አይጡና ዶሮው ከብቶቹን በሙሉ ወስደው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ዶሮው “ከላሞቹ አንዷን ለምን አናርዳትም?” አለ፡፡
አንዷንም ላም አርደው ሲያበቁ ዶሮው “አሁን ያለንን ሃብትና የከብቶች ብዛት ለማሳት እኔ የታረደችውን ላም ተረፈ ምርት ለብሼ ያሉንን የከብቶች ብዛት ሳሳይ አንተም የተወሰነ ስብ ወስደህ ትከሻህ ላይ በማኖር ማሳየት አለብን፡፡” አለው፡፡
በመቀጠልም ዶሮው “አሁን ወደ ተራራው ጫፍ ወጥተህ ለምን ለሁሉም አትታያቸውም?” አለው፡፡
አይጡም ወደተራራው አናት ላይ ሲወጣ በዚያው ቅፅበት ያየው አንድ ጭልፊት አይጡ የተሸከመውን ስብ ስላስተዋለ አንዴ ወደታች ተወርውሮ አይጡን ጨልፎት ሄደ፡፡ በመጨረሻም የብዙ ከብቶች ባለቤት የሆነው ዶሮ ወደመንደሩ በኩራት ተመለሰ፡፡
የዚህ ታሪክ መልዕክትም አንድ ሰው ከተጠቃ ጥቃቱ ወደራሳችንም ስለሚመጣ ከሌሎች ስህተት መማር አለብን የሚል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|