አባ ቦሎና የአንገት ጌጡ
በቦንሳሞ ሚኤሶ የተተረከ
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ልጃገረድ ውሃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ስትወርድ ወጣቱና ጠንካራው ቦሎ አያት፡፡ እርሱም “አንገትሽ ላይ ያደረግሽውን መቁጠሪያ ልየው፡፡” አላት፡፡
ከዚያም አይቶ፣ አይቶ ሲያበቃ መቁጠሪያውን ወንዙ ውስጥ ወረወረው፡፡ ልጅቷም በጣም አዝና ወደ ቦሎ አባት በመሄድ ለአባቱ “አባ ቦሎ ሆይ፣ ልጅህ የአንገት ጌጤን ወንዝ ውስጥ ወርውሮብኛልና ግረፍልኝ፡፡” አለችው፡፡
አባ ቦሎም “አይ አልመታውም፡፡” አላት፡፡
በዚህ ጊዜ ልጅቷ ወደ አንድ የዛፍ ጉቶ በመሄድ “አንተ የዛፍ ጉቶ ሆይ፣ አባ ቦሎ በዚህ ሲያልፍ ጠልፈህ ጣለው፡፡” አለችው፡፡ የዛፉም ጉቶ “አይሆንም፣ ለምንድነው ይህንን የማደርገው? አባ ቦሎን ለምንድነው ጠልፌ የምጥለው?” አላት፡፡
ልጅቷም “ምክንያቱም ቦሎ የአንገት ጌጤን አይቶ፣ አይቶ ሲያበቃ ወንዙ ውስጥ ስለጣለብኝ አባ ቦሎ እንዲገርፍልኝ ብጠይቀው እምቢ አለኝ፡፡” አለች፡፡
የዛፉንም ጉቶ “እኔም አላደርገውም፡፡” አላት፡፡
ከዚያም ልጅቷ ወደ ምስጥ ኩይሳ ሄዳ ለምስጡ “እባክህ የጉቶውን ሥር በልተህ ጉቶው እንዲሞት አድርገው፡፡” አለችው፡፡
ምስጡም “ለምንድነው ይህንን የማደርገው?” አላት፡፡
እሷም “ምክንያቱም ጉቶው አባ ቦሎን አልጠልፈውም አለኝ፡፡ አባ ቦሎም ልጁ የአንገት ጌጤን አይቶ፣ አይቶ ወንዝ ውስጥ በመወርወር አልመልስልሽም ያለኝን ቦሎን አልገርፍልሽም ስላለኝ ነው፡፡” አለችው፡፡
ምስጡም “አይ አላደርገውም፡፡” አላት፡፡
ከዚያም ልጅቷ ወደ አንድ ድመት ሄዳ “እባክሽ ምስጡን ብይው፡፡” አለቻት፡፡
ድመቷም “ለምንድነው ምስጡን የምበላው?” አለቻት፡፡
ልጅቷም “ምክንያቱም የጉቶውን ሥር አልበጥሰውም አለኝ፡፡ ጉቶውም አባ ቦሎን አልጠልፈውም አለኝ፡፡ አባ ቦሎም ልጁን አልገርፈውም አለ፡፡ ልጁም የአንገት ጌጤን ወስዶ አይቶ፣ አይቶ ሲያበቃ ከመመለስ ይልቅ ወንዙ ውስጥ ወረወረብኝ፡፡” አለቻት፡፡
ድመቷም “አይ ምስጡን አልበላውም አለቻት፡፡
ልጅቷም በመቀጠል ሰዎች አገኘችና “እባካችሁ ድመቷን ግደሏት፡፡” አለቻቸው፡፡
ሰዎቹም “ለምንድነው ድመቷን የምንገድላት?” አሏት፡፡
ልጃገረዷም “ምክንያቱም ድመቷ ምስጡን አልበላም አለች፡፡ ምስጡም የጉቶውን ሥር አልበጣጥስም አለኝ፡፡” ጉቶውም አባ ቦሎን አልጠልፈውም አለኝ፡፡ ቦሎም የአንገት ጌጤን አይቶ፣ አይቶ ሲያበቃ እንደመመለስ ወረወረብኝ፡፡” አለቻቸው፡፡
ሰዎቹም “ድመቷን አንገድላትም፡፡” አሏት፡፡
ከዚያም ወደ እሳት ሄዳ “እሳት ሆይ፣ እባክህ ሰዎቹን ከነጎጇቸው አቃጥላቸው፡፡” አለችው፡፡
እሳቱም “ሰዎቹን ጎጇቸው ውስጥ እንዳሉ ለምንድነው የማቃጥላቸው?” ብሎ ጠየቃት፡፡
እሷም “ምክንያቱም ሰዎቹ ድመቷን አንገድላትም አሉ፡፡ ድመቷም ምስጡን አልገድልም አለች፡፡ ምስጡም የጎቶውን ስር አልበጣጥስም አለ፡፡ ጉቶውም አባ ቦሎን አላደናቅፈውም አለ፡፡ አባ ቦሎም ቦሎን አልመታውም አለ፡፡ ቦሎም የአንገት ጌጤን አይቶ፣ አይቶ ሲያበቃ እንደመመለስ ወንዙ ውስጥ ወረወረብኝ፡፡” አለችው፡፡
እሳቱም “አላደርገውም” አላት፡፡ ከዚያም ወደ ውሃ ሄዳ “ውሃ ሆይ፣ እባክህ እሳቱን አጥፋው፡፡” አለችው፡፡
ውሃውም “እሳቱን ለምንድነው የማጠፋው?”ብሎ ጠየቃት፡፡
እሷም “ምክንያቱም እሳቱ ሰዎቹን አላቃጥልም አለ፡፡ ሰዎቹም ድመቷን አንገድላትም አሉ፡፡ ድመቷም ምስጡን አልበላውም አለች፡፡ ምስጡም የጉቶውን ሥሮች አልበጣጥስም አለ፡፡ ጉቶውም አባ ቦሎን አላደናቅፈውም አለ፡፡አባ ቦሎም ቦሎን አልመታውም አለ፡፡ ቦሎም የአንገት ጌጤን አይቶ፣ አይቶ እንደመመለስ ወደ ወንዙ ውስጥ ወረወረብኝ፡፡” አለችው፡፡
ውሃውም “አይሆንም! ጥፊ ከዚህ!” አላት፡፡
ከዚያም ወደ ዝሆን ሄዳ “አንተ ዝሆን ሆይ፣ እባክህ ውሃውን ሁሉ ጠጥተህ ጨርሰው፡፡” አለችው፡፡
ዝሆኑም “ለምንድነው ውሃውን በሙሉ የምጠጣው?” አላት፡፡
እሷም “ምክንያቱም ውሃው እሳቱን አላጠፋም አለ፡፡ እሳቱም ሰዎቹን አላቃጥላቸውም አለ፡፡ ሰዎቹም ድመቷን አንገድላትም አሉ፡፡ ድመቷም ምስጡን አልበላም አለች፡፡ ምስጡም የጉቶውን ሥራ ሥሮች አልበጣጥስም አለ፡፡ ጉቶውም አባ ቦሎን አልጠልፈውም አለ፡፡ አባ ቦሎም ቦሎን አልመታውም አለ፡፡ ቦሎም የአንገት ጌጤን ወስዶ አይቶ፣ አይቶ እንደመመለስ ወደ ወንዙ ውስጥ ጣለብኝ፡፡” አለችው፡፡
ዝሆኑም “ውሃውን ሁሉ አልጠጣውም፡፡” አላት፡፡
ከዚያም ወደ እረኞች ሄዳ “እባካችሁ ዝሆኑን ግደሉት፡፡” አለቻቸው፡፡
እረኞቹም “አይሆንም፣ ዝሆኑን አንገድለውም፡፡ ለምንድነው የምንገድለው?” ብለው ጠየቋት፡፡
ልጅቷም “ተመልከቱ፣ ዝሆኑ ውሃውን በሙሉ አልጠጣውም አለኝ፡፡ ውሃውም እሳቱን አያጠፋም፡፡ እሳቱም ሰዎቹን አያቃጥላቸውም፡፡ ሰዎቹም ድመቷን አይገድሏትም፡፡ ድመቷም ምስጡን አትበላውም፡፡ ምስጡም የጉቶውን ሥራ ሥሮች አይበጣጥሳቸውም፡፡ ጉቶውም አባ ቦሎን ጠልፎ አይጥለውም፡፡ አባ ቦሎም ቦሎን አይገርፈውም፡፡ ቦሎም የአንገት ጌጤን አይቶ፣ አይቶ ሲያበቃ እንደመመለስ ወደ ወንዙ ውስጥ ጣለብኝ፡፡” አለቻቸው፡፡
እረኞቹም “ዝሆኑን አንገድለውም፡፡” አሏት፡፡
ከዚያም ወደ ዛፉ ሄዳ “አንተ ዛፍ ሆይ እባክህ እረኞቹ ላይ ውደቅባቸው፡፡” አለችው፡፡
ዛፉም “ለምንድነው ይህንን የማደርገው? “አላት፡፡
ልጅቷም “ምክንያቱም እረኞቹ ዝሆኑን አይገድሉትም፡፡ ዝሆኑም ውሃውን በሙሉ አይጠጣውም፡፡ ውሃውም እሳቱን አያጠፋውም፡፡ እሳቱም ሰዎቹን አያቃጥላቸውም፡፡ ሰዎቹም ድመቷን አይገድሏትም፡፡
ድመቷም ምስጡን አትበላውም፡፡ ምስጡም የጉቶውን ሥራሥሮች አይበጣጥሳቸውም፡፡ ጉቶውም አባ ቦሎን ጠልፎ አይጥለውም፡፡ አባ ቦሎም ቦሎን አይመታውም፡፡ ቦሎም የአንገት ጌጤን አይቶ፣ አይቶ ሲያበቃ እንደመመለስ ወደ ወንዙ ወረወረብኝ፡፡” አለችው፡፡
ዛፉም “አይ እረኞቹ ላይ አልወድቅባቸውም፡፡” አላት፡፡
ከዚያ ልጅቷ ወደ መጥረቢያ ዘንድ ሄዳ “እባክህ ዛፉን ቆርጠህ ጣለው፡፡” አለችው፡፡
መጥረቢውም “ምንድነው ችግሩ? ምን አደረገሽ?” ብሎ ጠየቃት፡፡
ልጅቷም “እንግዲህ አየህ፣ዛፉ እረኞች ላይ አይወድቅባቸውም፡፡ እረኞቹም ዝሆኑን አይገድሉትም፡፡ዝሆኑም ውሃውን በሙሉ አይጠጣውም፡፡ ውሃውም እሳቱን አያጠፋውም፡፡ እሳቱም ሰዎቹን አያቃጥላቸውም፡፡ ሰዎቹም ድመቷን አይገድሏትም፡፡ ድመቷም ምስጡን አትበላውም፡፡ ምስጡም የጉቶውን ሥራሥሮች አይበጣጥሳቸውም፡፡ ጉቶውም አባ ቦሎን ጠልፎ አይጥለውም፡፡ አባ ቦሎም ቦሎን አይመታውም፡፡ ቦሎም የአንገት ጌጤን አይቶ፣ አይቶ ሲያበቃ እንደመመለስ ወደ ወንዙ ወረወረብኝ፡፡” አለችው፡፡
መጥረቢያውም “እንዴት ያሳዝናል! ምንም አታስቢ ቆንጆ ልጅ እረዳሻለሁ፡፡” አላት፡፡
ከዚያም መጥረቢያው ዛፉን ሲያሳድድ፣ዛፉ እረኞቹን ሲያሳድድ፣ እረኞቹም ዝሆኑን ሲያሳድዱ፣ ዝሆኑም ውሃውን ሲያሳድድ፣ ውሃውም እሳቱን ሲያሳድድ፣ እሳቱም ሰዎቹን ሲያሳድድ፣ ሰዎቹም ድመቷን ሲያሳድዱ፣ ድመቷም ምስጡን ስታሳድድ፣ ምስጡም የጉቶውን ስሮች ሲያሳድድ፣ ጉቶውም አባ ቦሎን ሲያደናቅፈው፣ አባ ቦሎም ልጁን ሲያሳድድ፣ ልጁም ወደ ወንዙ ሄዶ የአንገት ጌጡን አወጣው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|