ተኩላና ጥንቸል
በመሃመድ ኩዩ የተተረከ
ከእለታት አንድ ቀን አንድ ተኩላ ምግብ ለመፈለግ በየአለቱ ሥር ሲንፏቀቅ አንድ ትልቅ ቋጥኝ እግሩ ላይ ተጭኖበት ከመሬት ጋር አጣበቀው፡፡ ቢጎትት፣ ቢጎትት፣ በአፉም ቢግጥ፣ ቢግጥ እግሩን ማላቀቅ አልቻለም፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ታዲያ አንዲት ጥንቸል በዚያ ስታልፍ አይቶ “ጥንቸል ሆይ፣ እባክሽ እርጂኝ፡፡ ይህንን ቋጥኝ ከላዬ ላይ አንስተሸ እግሬን አላቂልኝ፡፡” አላት፡፡
ጥንቸሏም “እኔ ደካማ ነኝ፡፡ ይህንን ቋጥኝ ለማንቀሳቀስም ብዙ ጊዜ ይፈጅብኛልና ከቋጥኙ ባላቅቅህ ግን ምን ታደርግልኛለህ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
ተኩላውም “ለዚህ አታስቢ፤ እስክትፈነጂ ድረስ አበላሻለሁ፡፡ ምንም መብላት እስኪሳንሽ ድረስ እመግብሻለሁ፡፡” አላት፡፡
ጥንቸሏም ቋጥኙን ገፍታ፣ ገፍታ በመጨረሻ ማንቀሳቀስ ቻለች፡፡ ነገር ግን ተኩላው ገና ነፃ ከመውጣቱ ዘሎ ጥንቸሏን ከያዛት በኋላ “አሁን እበላሻለሁ፡፡” አላት፡፡
ጥንቸሏም “ይህማ በፍፁም አይቻልም፡፡ ከወጥመድ ያዳነህን ሰው እንዴት ትበላለህ?” አለችው፡፡
ተኩላውም “ሙሉ ቀን ምንም ምግብ አልበላሁምና የምበላው ነገር ያስፈልገኛል፡፡” አለ፡፡
ጥንቸሏ በድጋሚ “እንደዚህማ አይሆንም፡፡ ወደ አገር ሽማግሌዎች ሄደን እነርሱ ትክክለኛውን ነገር ይወስኑ፡፡” አለች፡፡
ተያይዘውም ሲሄዱ ከአዛውንቶቹ አንዱን አግኝተው የመጡበትን ጉዳይ ነገሩት፡፡
አዛውንቱም ሰው አዳምጧቸው ሲጨርስ “በሉ የሆነውን ሁሉ በዝርዝር ንገሩኝ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም ሁሉንም ነገር አስረድተውት ሲጨርሱ ሽማግሌው “ተኩላው ተሳስቷልና ጥንቸሏ በነፃ መለቀቅ አለባት፡፡” ብሎ ፈረደ፡፡
በዚህ ጊዜ ተኩላው በጣም ስለተናደደ “ጥንቸሏን ብቻ ሳይሆን አንተንም እበላሃለሁ፡፡” አለ፡፡
ሽማግሌውም የደነገጠ በመምሰል “እንግዲያው ፍርዴ ተሳስቷል መሰለኝ፡፡ እስኪ ጉዳዩን እንደገና ፍርድ ልስጥበት፡፡ ማስረጃዎችን በሙሉ ሳልመለከት እንዴት ነው ፍርድ የሰጠሁት?” ማለት ጀመረ፡፡
ከዚያም “በሉ አሁን መጀመሪያ ወደተገናኛችሁበት ቦታ ውሰዱኝና የሆነውን ነገር በድርጊት ታሳዩኛላችሁ፡፡” ብሏቸው ወደ ስፍው ተያይዘው ከቦታው ሲደርሱ ሽማግሌው ሰው “እሺ እዚያ ጋ? ተኩላው በትክክል የት ጋ ነበር?” ብሎ ጠየቀ፡፡
ተኩላውም ተጋድሞ “እዚህ ጋ ነበርኩ” ሲል ሽማግሌው ሰው ጥንቸሏን “አንቺ ደግሞ ይህንን ቋጥኝ ነው የገፋሽው? ይህ የማይታመን ነገር ነው፡፡ እስኪ እንዴት እንደገፋሽው አሳይኝ፡፡” አላት፡፡
ጥንቸሏም ቋጥኙን ቀስ በቀስ ገፍታ የተኩላው እግር ላይ አሳረፈችው፡፡
ሽማግሌውም ሰው “እናም በዚህ ሁኔታ ነው ተኩላውን ያገኘሽው?” ብሎ ጥንቸሏን ጠየቃት፡፡
ጥንቸሏም “አዎን” አለች፡፡
ሽማግሌውም ሰው ወደ ተኩላው ዞር ብሎ “እርግጠኛ ነህ በዚህ ሁኔታ ነው ጥንቸሏ ያገኘችህ?” አለው፡፡
ተኩላውም “አዎን” አለ፡፡
አዛውንቱም ሰው “መልካም፣ ጉዳዩ እዚህ ላይ ያበቃል፡፡ ጥንቸል ሆይ፣ አንቺም ወደ መጣሽበት ሂጂ፣ እኔም ወደነበርኩበት እመለሳለሁ፣ ተኩላውንም የነበረበት እንተወዋለን፡፡” ብሎ ፈረደ ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|