ጅብና አህያ
በሁሴን ቱሲ የተተረከ
ከእለታት አንድ ቀን የአንድ የጅብ ግልገል ሞቶ ትልቅ የሃዘን ስርአት ስለነበረ ሁሉም እንስሳት ጅቡን ሊያስተዛዝኑ በመሄዳቸው በሃገሩ ባህል መሰረት አህዮችም ለጅቡ ያላቸውን ክብር ለመግለፅ ሄዱ፡፡
ወደ ጅቡም ቤት በመሄድ በባህሉ መሰረት ማልቀስና የሃዘን እንጉርጉሮ ማሰማት ጀመሩ፡፡
እንደዚህም አሉ ”ታላቁ ልጅህን ምን ገደለው? ማነው የገደለው? ይህን ታላቅ ሃዘን ምንድነው ያመጣብህ?”
ጅቦቹም እያለቀሱ “አሁን ያ ሁሉ አልፏል፡፡ ነገር ግን እናንተ ለእኛ ምን ምግብ ይዛችሁልን መጣችሁ?” አሏቸው፡፡
አህዮቹም “መቼም በባህላችን መሰረት ስለምንሰጣችሁ ነገር እንነጋገር፡፡” ብለው ሊመካከሩ ተነስተው ወደ ውጪ በመውጣት እንደዚህ ተባባሉ “አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አዋጥተው ለሃዘንተኛው ቤተሰብ የሚበላ ነገር ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን ጅቦቹ እኛን ሊበሉን እንደሚፈልጉ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ምን እናድርግ?”
ከዚያም “ሁላችንም ማምለጥ አለብን፡፡ ሆኖም ከመሀከላችን አንዲት አህያ ልከን ‘ይህንን ነው እንድትበሉ ያመጣንላችሁ’ እንድትላቸው አድርገን አህያዋ እንዴት ማምለጥ እንዳለባት ሹክ እንላታለን፡፡” አሉ፡፡
በዚህ ዓይነት አንዲት አህያ ልከው አህያዋ ወደ ጅቦቹ ጋ ስትገባ ጅቦቹ አይተዋት “ይህችን በኋላ እንበላታለን፡፡” ተባባሉ፡፡
እሷም “እሺ፣ እኔ ስጦታችሁ ነኝ፡፡” አለች፡፡
ከጥቂት ቆይታም በኋላ አህያዋ “እስኪ ተነስቼ ዞር፣ ዞር ልበል፡፡” ስትል ጅቦቹ “እሺ፣ ነገር ግን ብዙ ርቀሽ አትሂጂ፡፡ ስንፈልግሽስ እንዴት ነው የምንጠራሽ?” አሏት፡፡
አህያዋም “ይህማ ችግር የለውም፡፡ የቀድሞዋ! የቀድሞዋ! እያላችሁ ከተጣራችሁ እኔ እየሮጥኩ እመጣለሁ፡፡” አለቻቸው፡፡
በዚህ ሁኔታ ጅቦቹ ስለራባቸው “የቀድሞዋ! የቀድሞዋ! ወዴት ሄድሽ? ተመለሺ!” እያሉ ተጣሩ፡፡
እሷም በሩቅ ሆና “የቀድሞዋ ሄዳ ጋጣዋ ውስጥ ያሉትን ሃዲድ ብረቶች እያሸተተች ነው፡፡” ብላ መለሰች፡፡
በዚህ ጊዜ ጅቦቹ በጣም ተቆጥተው “ከያዝንሽ እንበላሻለን!” አሏት፡፡
አህያዋ ግን ከት ብላ ስቃ “ከዚህ በኋላ በፍፁም አላመሽም፡፡” አለቻቸው ይባላል፡፡
ታዲያ አሁንም ከከብቶችና በጎች ሁሉ ቀድመው አህዮች ወደ ጋጣቸው የሚገቡት በዚህ ምክንያት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|