አይጥና እንቁራሪት
በቦንሳሞ ሚኤሶ የተተረከ
ከእለታት አንድ ቀን አንድ አይጥ ከእቁራሪት ጋር ተገናኝቶ ጓደኛሞች ለመሆን በመስማማት ጓደኝነት መሠረቱ፡፡
አብረውም ሙሉ ቀን ሲዞሩ መዋልና ሌሎች ጓደኞች መመስረት ጀመሩ፡፡ በኋላም አይጡ እንቁራሪቱን ለመጋበዝ ፈልጎ ወደ ቤቱ ይዞት በመሄድ በእንግድነት ክብር ያከማቸውን ሁሉ አውጥቶ ጋበዘው፡፡ ጥራጥሬ፣ ገብስ፣ ስንዴና ሌሎች የእህል ዓይነቶችንም አቀረበለት፡፡
በመጀመሪያ እንቁራሪቱ አንዲት የስንዴ ፍንካች ሊውጥ ሲሞክር ገለባው ጎሮሮውን ስለቧጠጠው “ይህ ምን አይነት የማይረባ እሾሃማ ምግብ ነው! ሌላ ምግብ የለህም?” አለው፡፡
ከዚያም አይጡ ሽንብራ ሰጠው፡፡ እንቁራሪቱም ሽንብራውን በአፉ ውስጥ ትንሽ ካንከባለለው በኋላ አልሟሟ ስላለው መልሶ ተፋው፡፡ እናም አይጡን “ይህ እንዴት ያለ ደረቅ ምግብ ነው! ጥሩ ምግብ አይደለም፡፡ ሌላ ለስላሳ ምግብ የለህም?” አለው፡፡
አይጡም “የለኝም፡፡ እኛም ጠንካራና ብርቱ የሆነው ጠንከር ያለ ምግብ በመብላታችን ነው፡፡” አለው፡፡
ከዚያም በሌላኛው ቀን ወደ እንቁራሪቱ ቤት ለመሄድ ወስነው ወደዚያው ሲሄዱ እንቁራሪቱ የሚኖረው በኩሬ ውስጥ ስለነበረ ዘሎ ውሃው ውስጥ ገብቶ አይጡን ይጠራው ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ አይጡም ውሃው ውስጥ ዘሎ ገባ፡፡ ሆኖም መዋኘት አይችልም ነበርና ወዲያው መንቦጫረቅና ውሃው ውስጥ ማጣጣር ጀመረ፡፡
እንቁራሪቱም “እንዴት ይገርማል! ገና ሳትጠጣ ሰከርክ እንዴ? እኔ እኮ ብዙ ምግብና መጠጥ ልሰጥህ አስቤ ነበር፡፡” አለው፡፡
ከዚያም አይጡን ወደ ኩሬው አፋፍ ላይ ገፍትሮ አውጥቶት ያከማቸውን ምግብ ሁሉ ይዞለት መጣ፡፡ ብዙ ትላትሎችና ነፍሳትን አምጥቶለት አይጡ ሁሉንም አፉ ውስጥ ጨምሮ ቢያጣጥማቸው ምንም ቅመም ስላልነበረው ምግቡ ውሃ፣ ውሃ አለው፡፡
በዚህ ጊዜ “ምን አይነት የማይረባ ምግብ ነው! እንዴት ነው ይህንን የምትመገበው?” ብሎ እንቁራሪቱን ጠየቀው፡፡ እንቁራሪቱም “እኛ ደግሞ ለስላሳና ሙልጭልጭ የሆነው ይህንን ስለምንመገብ ነው፡፡” አለው ይባላል፡፡
የዚህ ታሪክ ሁለት ትርጉሞች “ሰው የሚመስለው ምግቡን ነው፡፡” የሚልና “ከማይመስሉህ ሰዎች ጋር አትዋል” የሚል ናቸው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|