የውሻ ፀብ
በመሃመድ ኩዩ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሮበሌ መግራ የተባለ አንድ በጣም ብልህ ሰው ነበረ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ የጎረቤቶቹ ንብረት የሆኑ ሁለት ውሾች ሲጣሉ አይቶ “እባካችሁ እነዚህን ሁለት ውሾች ገላግሏቸው፤ ካለበለዚያ ልጆቹም መጣላት ይጀምራሉ፡፡” አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ ስቀውበት ዝም ሲሉ ከጥቂተ ደቂቃዎች በኋላ አንዱ ልጅ ከአንደኛው ቤት ወጥቶ ሁለቱ ውሾች ሲጣሉ ባየ ጊዜ አንደኛውን ውሻ በዱላ መታው፡፡ በዚያው ቅፅበት ሌላኛው የጎረቤት ልጅ ከቤቱ እየወጣ ስለነበር የራሱ ውሻ በዱላ ሲመታ ሲያይ “ምን ብትደፍረኝ ነው ውሻዬን የምትመታው?” በማለት ሁለቱ ልጆች መደባደብ ጀመሩ፡፡
ይህንን ያየው ሮበሌ መግራ “እባካችሁ እነዚህን ልጆች ገላግሏቸው፡፡” ካለበለዚያ እናቶቻቸው መደባደባቸው አይርቀርም፡፡” አለ፡፡
ብዙም ሳይቆይ አንደኛዋ እናት ከቤቷ ወጥታ ልጇን እየደበደበ ያለውን ልጅ መታችው፡፡ ከዚያም የተመታው ልጅ እናት ደግሞ ወጥታ “እንዴት ብትደፍሪኝ ነው ልጄን የምትመቺው?” ብላ ሁለቱ እናቶች እርስ በርስ መደባደብ ጀመሩ፡፡
አሁንም ሮበሌ መግራ አግድም እየተመከተ “እባካችሁ እነዚያን ሴቶች ገላግሏቸው፤ ካለበለዚያ ባሎቻቸው መደባደብ ይጀምራሉ፡፡” አለ፡፡
አሁንም ማንም አልሰማውም፡፡ ሆኖም ወዲያው አንደኛው ባል ወጥቶ ሚስቱ እየተደበደበች መሆኑን ባየ ጊዜ ደብዳቢዋን መምታት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የሌላኛዋ ሴት ባል ወጥቶ ሲመለከት ሚስቱ በሌላ ወንድ ስትደበደብ ሲያይ እርሱም ድብድቡን ተቀላቀለ፡፡
አዛውንቱም ሰው እንደገና “እባካችሁ እነዚህን ወንዶች ገላግሏቸው፤ ካለበለዚያ ጎሳዎቻቸው መጣላት ይጀምራሉ፡፡” አለ፡፡
አሁንም ማንም አልሰማውም ነበርና ወዲያው የሁለቱ ሰዎች ጎሳዎች በመሃከላቸው ትንሽ ጦርነት ፈጠሩ፡፡ በጦርነቱም ከእያንዳንዱ ወገን ስምንት ሰዎች ሞቱ፡፡ ከዚያም የሃገር ሽማግሌዎች ተጠርተው ግጭቱን እንዲፈቱ ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ በሃገሬው ባህል መሰረት ከአንደኛው ጎሳ ለተገደለ አንድ ሰው ከሌላኛው ጎሳ አንድ ሰው መገደል ወይም አንድ መቶ ከብቶች በካሳ መከፈል ነበረበት፡፡
ይህ በመሆኑ የሃገር ሽማግሌዎቹ ጉማ በሚባለው የባህል የፍትህ ሥርአት ላይ ተቀምጠው “ለእያንዳንዱ ለተገደለ ሰው መቶ ከብቶች ካሳ መስጠት ካለባቸው ከእያንዳንዱ ወገን ስምንት መቶ ከብቶች ለካሳ በመፈለጋቸው በአጠቃላይ 1600 ከብቶች ማለት ሲሆን ይህም ማለት ከብቶቹ በሙሉ መሄዳቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስምንት ሰዎች ከእያንዳንዱ ወገን መገደል ካለባቸው በድምሩ 16 ተጨማሪ ሰዎች ሊገደሉ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በአጠቃላይ 32 ሰዎችን ማጣት ማለት ነውና ይህ ለሁላችንም ትልቅ ሃዘን ነው፡፡ ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም፡፡” እያሉ መምከር ጀመሩ፡፡
በዚህ ጊዜ አንድ እብድ ብልህ አዛውንት ሰው በአካባቢው ያልፍ ነበርና “ይህ ሁሉ ችግር ምንድነው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
እነርሱም “በጣም ትልቅ ችግር ገጥሞናል፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ውሾች ተጣሉ፡፡ ከዚያም የውሾቹ ባለቤት የሆኑ ሁለት ልጆች ተጣሉ፡፡ ቀጥሎ የልጆቹ እናቶች ተደባደቡ፡፡ ከዚያም ባሎቻቸው በመደባደባቸው የሁለቱ ሰዎች ጎሳዎች የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ስለገቡ 16 ሰዎች ማለትም ከእያንዳንዱ ወገን 8 ሰዎች ለህልፈት ተዳረጉ፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ አገር ሽማግሌዎች ብንመጣም ሽማግሌዎቹ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል፡፡ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሟች መቶ ከብቶች መክፈል ወይም ከሌላው ወገን አንድ ሰው መግደል አለብን፡፡ ይህ ማለት ደግሞ 1600 ከብቶችን መክፈል ወይም የሌሎች 16 ሰዎችን ህይወት ማጥፋት ሊኖርብን ነው፡፡” አሉት፡፡
አዛውንቱም እብድ ብልህ ሰው ይህንን ሁሉ ካዳመጠ በኋላ “አዳምጡኝ! ስምንት፣ ስምንት መቶ ከብቶችን መክፈል ካለባችሁ በድምሩ 1600 ከብቶች ማለት ለእናንተ ኪሳራ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከእያንዳንዱ ወገን ስምንት፣ ስምንት ሰው ቢገደል ከሞቱት 16 ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች 16 ሰዎችን ማጣታችሁ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በድምሩ የ32 ሰዎች ህይወት መጥፋት በመሆኑ ይህም እጅግ ትልቅ ሃዘን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ መፍትሄ ልስጣችሁ፡፡” አለ፡፡
እነርሱም “አዎ! መፍትሄህ ምንድነው?” አሉት፡፡
እርሱም “ሁላችሁም ሜታ ተብሎ የሚጠራውን ከብር የተሰራ የአንገት ጌጥ ከሁለቱም ወገን ወስዳችሁ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፡፡ ከዚያም ያለፈውን ሁሉ ረስታችሁ እርስ በርስ ይቅር ተባባሉ፡፡” አላቸው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|