እሳት፣ውሃ፣እውነትና ሃሰት
በመርጋ ደበሎ የተተረከ
እሳት፣ ውሃ፣ እውነትና ሃሰት ጓደኞች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሃሰት በዚህ ጥምረት ደስተኛ ስላልነበረ አንድነታቸውን ማበላሸት ፈልጎ እንዲህ አለ “ለምን ወደ አንድ ስፍራ ተጉዘን እያንዳንዳችን የራሳችንን ግዛት አንመሰርትም? ስለዚህ ተነስተን አብረን እንጓዝ፡፡”
ሁሉም በሃሳቡ ተስማምተው ሲሄዱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሀሰት ወደ ውሃ ጠጋ ብሎ “እሳት ሣሩን፣ ደኑንና ቁጥቋጦውን የሚያቃጥል ቀንደኛ ጠላታችን ስለሆነ ለምንድነው ከእርሱ ጋር ግዛት ፍለጋ የምንሄደው?” አለው፡፡
ውሃም “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለ፡፡
ሃሰትም ቀበል አድርጎ “ልንገድለው እንደሚገባ ግልፅ ነው፡፡ እሳትን የማጥፋት ብቸኛ ኃይል ያለህ ደግሞ አንተ ነህ፡፡ እናም ቁጭ ሲል ጠብቀህ እላዩ ላይ ራስህን በመርጨት አጥፋው፡፡” አለው፡፡
ውሃም “ራሴን መሬቱ ላይ ከረጨሁ ተመልሼ ውሃ መሆን አልችልም፡፡” አለ፡፡
ሀሰትም “ችግር የለውም፡፡ ተረጭተህ እንዳትበታተን የተወሰኑ ድንጋዮች በዙሪያህ አኖርና በኋላ እሰበስብሃለሁ፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ያልጠረጠረው እሳት መጥቶ ቁጭ ሲል ውሃው አንድ ጊዜ በላዩ ላይ ሲረጭ ሃሰት ድንጋዮች ዙሪያውን አድርጎ ውሃውን ከሰበሰበውና እሳትን ካስወገዱ በኋላ አብረው መጓዝ ጀመሩ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሃሰት ውሃውን “ለምን እዚህ ገደል አፋፍ ላይ ቁጭ ብለህ በተፈጥሮ ውበት አትዝናናም?” አለው፡፡
ውሃም አፋፉ ላይ ቁጭ ሲል ሃሰት ቀስ ብሎ ተነስቶ ውሃ የተቀመጠባቸውን ድንጋዮች ከስሩ ሲለቅማቸው ውሃው በመረጨት በዚያው ተበታትኖ ጠፋ፡፡
በመጨረሻም ሃሰት እውነትን ማጥፋት ነበረበትና ወደ አንድ ትልቅ ተራራ በተቃረቡ ጊዜ ሃሰት እውነትን ከተራራው ግርጌ ቁጭ በል ብሎት ከተራራው አናት ላይ ትልቅ አለት ቁልቁል በመልቀቅ እውነትን ሊጨፈልቀው ሲል እውነት ቀልጠፍ ብሎ ማምለጥ በመቻሉ አለቱ ተንከባሎ ሲፈረካከስ ከውስጡ አልማዝ፣ ወርቅና ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድናት ወጡ፡፡ ሃሰትም የእውነትን አስከሬን ሊመለከት በመጣ ጊዜ እነዚህን ሁሉ የከበሩ ድንጋዮች አየ፡፡
እናም “እነዚህ ሁሉ ከየት መጡ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
እውነትም “አለቱ እላዬ ላይ ሲወድቅ እነዚህ ማዕድናት ወጡ፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ሃሰት “አሁን ደግሞ እኔ ከተራራው ግርጌ ልቀመጥና አንተ አለቱን በላዬ ላይ ልቀቅብኝ፡፡” አለው፡፡
እናም እውነት ወደ ተራራው ጫፍ ወጥቶ ትልቅ አለት ወደታች በለቀቀ ጊዜ አለቱ የሃሰት አናት ላይ አርፎ ሃሰትን ጨፈላልቆ ገደለው፡፡
ይህ የሚያሳየው እውነት ፈተና ቢገጥመውም በመጨረሻ አሸናፊ መሆኑን ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|