ብልሁ ወንድም
በመርጋ ደበሎ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሶስት ወንድ ልጆች የነበሩት አባት ነበር፡፡ ታዲያ ከሶስቱ በዕድሜ ትንሹ በጣም ብልህ ስለነበረ አባትየው አብልጦ ይወደው ነበር፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ ሁለቱ ወንድሞቹ በትንሹ ወንድማቸው ይቀኑበት እንደነበር አባትየው ስለሚያውቅ ሲሞት ከብቶቹን በሙሉ ለሁለቱ ታላላቅ ልጆቹ ሲያወርስ ለትንሹ ልጅ ግን አንድ በሬ ብቻ ትቶለት ሞተ፡፡
ሆኖም ታላላቅ ወንድሞቹ ትንሹ ወንድማቸው ባገኘው አንድ በሬ እንኳን ቀንተው አንድ ቀን “በሬህን ማረድ አለብን፡፡” ሲሉት ታናሻቸው ስለነበረ እምቢ ማለት አልቻለም፡፡
እናም “እንግዲያው እንደዚያ ከሆነ እኔ ምንም ማድረግ አልችልምና ቆዳውን ብቻ ስጡኝ፡፡” አላቸው፡፡
በሬውንም አርደው ሲጨርሱ ትንሹ ወንድማቸው ቆዳውን ወስዶ ካደረቀው በኋላ ሲመሽ ወደ ገበያ ወስዶ ከአንድ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ቀኑም በጣም እየመሸ ሲሄድ የተወሰኑ ነጋዴዎች ዛፉ ስር ለመተኛት መጡ፡፡ እኩለ ሌሊት በሆነም ጊዜ ትንሹ ወንድም ተነስቶ ቆዳውን በዱላ መቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ደንግጠው ከእንቅልፋቸው የባነኑት ነጋዴዎች ዛፉን መብረቅ የመታው ስለመሰላቸው የያዙትን ዕቃ በሙሉ ጥለው ሸሹ፡፡ ከዚያም ልጁ እቃቸውን ወስዶ ወደ ወንድሞቹ ይዞ ሄደ፡፡
እነርሱም “ይህንን ሁሉ ዕቃ ከየት አገኘህ” ብለው ሲጠይቁት “የቆዳ ዋጋ እጅግ ስለናረ ይህንን ሁሉ ዕቃ ያገኘሁት በአንድ ቆዳ ምትክ ነው፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ወንድሞቹ ከብቶቻቸውን በፍጥነት ካረዱ በኋላ ቆዳውን ወደ ገበያ ይዘው ሄደው “አለ ቆዳ የሚሸጥ! አለ ቆዳ የሚሸጥ!” እያሉ ቢጮሁም ገበያተኛው ሁሉ “የእናንተን ቆዳ አንፈልግም! እናንተ ደደቦች!” ብሎ አላገጠባቸው፡፡
በዚህም በጣም ተበሳጭተው ወንድማቸውን “ስላታለልከን እንደ ቅጣት ይሆንህ ዘንድ ጎጆህን እናቃጥላለን፡፡” አሉት፡፡
ብልሁም ወንድም “ያንን የምታደርጉ ከሆነ ምንም ማድረግ አልችልምና አመዱን ብቻ ስጡኝ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም ጎጆውን ካቃጠሉ በኋላ ልጁ አመዱን በስልቻ ሞልቶ ወደ አንድ ሃብታም ሰው ቤት ሄደ፡፡ ሃብታሙንም ሰው እንዲያሳድረው ሲጠይቀው ሰውየው ፈቀደለት፡፡
ከዚያም ለእራት በተጠራ ጊዜ “እነዚህ ስልቻዎች ብዙ ውድ ንብረቶች ስላሉባቸው ጠብቁልኝ፡፡” አላቸው፡፡
ከዚያም እራቱን በልቶ ወደ መኝታው ሄደ፡፡ በንጋታው ጠዋት ከእንቅልፉ ተነስቶ መጮህ በጀመረ ጊዜ ሃብታሙ ሰው ምን ሆኖ እንደሚጮህ ሲጠይቀው ልጁም ሰዎች ንብረቶቹን ሁሉ ወስደው ስልቻዎቹን በአመድ እንደሞሉበት ነገረው፡፡
ሃብታሙም ሰው ስሙና ክብሩ እንዲጎድፍ ስላልፈገለገ ልጁን “አንተ በፈለከው ነገር ስልቻዎችህን እሞላልሃለሁ፡፡” ብሎ ስልቻዎቹን በሙሉ በስንዴ፣ በጤፍና በመሣሰሉት ጥራጥሬዎች ሞላለት፡፡
ከዚያም እህሉን ጭኖ ወደ ቤቱ በመመለስ ለወንድሞቹ “አመድ በጣም በመወደዱ በምን ቀይሬው እንደመጣሁ ተመልከቱ፡፡” ብሎ ያመጣውን እህል አሳያቸው፡፡
ወንድሞቹም ጎጆዎቻቸውን ካቃጠሉ በኋላ አመዱን ወደ ገበያ ወስደው “አመድ የሚገዛ!” ብለው ሲጮሁ ሁሉም ሰው “እናንተ ደደቦች! አመድ ማን ይገዛል?” ብለው ተሳለቁባቸው፡፡ አሁን እጅግ በጣም ስለተበሳጩ ወንድማቸውን ሊገድሉት በማሰብ በቅርጫት ጠቅልለው ገደል ውስጥ ሊወረውሩት ወሰኑ፡፡
ተሸክመውትም ወደ ገደል አፋፍ እየወሰዱት ሳለ በመንገዳቸው ላይ አንድ አዛውንት ሰው መጥተው “ከብቶቼ ስለበረገጉብኝ እባካችሁ መልሱልኝ፡፡” ብለው ተማፀኗቸው፡፡
እናም ወንድሞቹ ቅርጫቱን አስቀምጠው ወደ ከብቶቹ ሲሮጡ ትንሹ ልጅ ከቅርጫቱ ውስጥ ሲጣራ ሰምተው አዛውንቱ “ምን ሆነሃል?” ብለው ጠየቁት፡፡
ልጁም “ንጉስ ካልሆንክ እያሉኝ ነው፡፡ እኔ ግን አልፈልግም፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ አዛውንቱ ሰው “እኔ ቅርጫቱ ውስጥ ብገባ ንጉስ እሆናለሁ?” ብለው ጠየቁት፡፡
ልጁም ፈጠን ብሎ “አዎን” አላቸው፡፡
ስለዚህ አዛውንቱ ሰው ልጁን ፈትተው ራሳቸው በቅርጫቱ ተጠቀለሉ፡፡ ወንድሞቹም ሲመለሱ ቅርጫቱን ተሸክመው ወስደው ገደል ውስጥ ወረወሩት፡፡
ከዚያም ትንሹ ልጅ ከብቶቻቸውን ሁሉ ወስዶ ወደቤት ሲመለስ ወንድሞቹ “እነዚህን ሁሉ ከብቶች ከየት አመጣህ?” ብለው ጠየቁት፡፡
እርሱም “ገደሉ ውስጥ ብዙ ከብቶች አሉ፡፡ እናንተም በቅርጫት ውስጥ ሆናችሁ ወደገደሉ ብትዘሉ ከብቶች ታገኛላችሁ፡፡” ሲላቸው ቅርጫት ውስጥ ገብተው ራሳቸውን ወደ ገደሉ ወርውረው ሲሞቱ እርሱ በሰላም መኖር ጀመረ፡፡
ይህ የሚያሳየው ክፉ ነገር በሌሎች ላይ ማድረግ ዞሮ በራስ ላይ እንደሚደርስ ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|