ድመቶችና አይጦች
በመርጋ ደበሎ የተተረከ
ድሮ፣ድሮ ድመቶችና አይጦች በህብረት አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ጓደኞችም ነበሩ፡፡ በኋላ ታዲያ አይጦች አንድ የሆነ ሴራ እየተጠነሰሰ መሆኑን ስለደረሱበት ቀስ በቀስ መጥፋት ጀመሩ፡፡ ጉዳዩንም ማጣራት ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም ድመቶቹ አይጦቹን እየበሏቸው መሆኑን ስለደረሱበት መደበቅ እንዳለባቸው አወቁ፡፡ ስለዚህ ጉድጓድ እየቆፈሩ መደበቅ ጀመሩ፡፡ እናት አይጦችም ልጆቻቸውን ወደ ድመቶች እንዳይሄዱ ሁልጊዜ ስለሚያስጠነቅቋቸው ከጊዜ በኋላ ድመቶቹ የሚበሉት ነገር አጡ፡፡
በዚህ ጊዜ ድመቶቹ ተሰባስበው “እንግዲህ አይጦች ስለጠፉ እንዴት አድርገን መያዝና መብላት እንችላለን?”ብለው ተማከሩ፡፡
ከዚያም አንድ እቅድ አውጥተው እቅዱም አይጥን ለጋብቻ በመጠየቅ በሰርጉ እለት አይጦቹን ሁሉ መብላት ነበር፡፡
ስለዚህ ሽማግሌ ድመቶችን ወደ አይጦቹ ሽማግሌዎች በመላክ ወንድ ልጃቸው ሴት ልጃቸውን እንዲያገባ አስጠየቁ፡፡
አይጦቹ ግን ትንሽ ስለተጠራጠሩ “አይ፣አይ፣አይ፣ የእውነታችሁን ስላልሆነና ስለምትበሉን ጋብቻውን አንፈልገውም፡፡” አሉ፡፡
ድመቶቹም “በፍፁም! ስላለፈው ነገር ይቅር በሉን፤ አሁን ግን እውነታችንን ነው፡፡ ጋብቻውን ብቻ ነው የምንፈልገው፡፡” አሉ፡፡
በሰርጉም እለት አይጦች አሁንም ሥጋት ላይ ስለነበሩ ልጆቻቸው ድመቶቹ ሲመጡ እንዲጠነቀቁ አሳሰቧቸው፡፡ ድመቶቹም ከሩቅ የሰርግ ዘፈን እየዘፈኑ መጡ፡፡
ወደ ሰርጉ ቦታም እየታቀረቡ ሲመጡ የሰርጉ ዘፈን ቃላት ተቀይረው
“ክበቡና ዋጧቸው! ክበቡና ዋጧቸው!” የሚሉ ሆኑ፡፡
አይጦቹም “ዝፈኑ ግን ድመቶቹን ተጠንቀቁ! ዝፈኑ ግን ድመቶቹን ተጠንቀቁ!” እያሉ ይዘፍኑ ጀመር፡፡
እናም አይጦቹ ድመቶቹ “ዋጧቸው!” እያሉ ሲዘፍኑ በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወደ ጉድጓዶቻቸው ዘለው በመግባት “ግን ተጠንቀቋቸው!” ብለው በመዝፈን አመለጡ፡፡
በሌላ ቀን የድመቶቹ ሽማግሌዎች ተመልሰው መጥተው “ወደ ሠርጉ ሥፍራ መጥተን ነበር፡፡ ነገር ግን ማናችሁም አልነበራችሁም፡፡” አሉ፡፡
አይጦቹም “አዎ ነገር ግን እኛም አውቀናል፣ ጉድጓድ ምሰናል፡፡” አሏቸው ይባላል፡፡
የዚህ ተረት መልዕክትም ችግር በመጣ ጊዜ ማምለጫ ዘዴ ማዘጋጀት እንዳለብን የሚያስተምረን ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|