እህትና ወንድም
በተስፋዬ ጪብሳ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ ባልና ሚስት ከወንድ ልጃቸው ጋር ይኖሩ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ሰውየው ነፍሰ ጡር ሚስቱን ትቶ ወደ ጦርነት ሊሄድ ተነሳ፡፡
ልጁንም ጠርቶት “አንድ ትልቅ ነገር እንድትሰራ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ በሌለሁበት ጊዜ ሁሉ እናትህን መንከባከብ የአንተ ኃላፊነት ነው፡፡ እናትህ ስትወልድ ግን አንድ ነገር እንድታደርግልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይኸውም የሚወለደውን ህፃን ተመልክተህ ሴት ልጅ ከሆነች ግደላትና ደሟን ጦር ሜዳ ድረስ አምጣልኝ፡፡ ነገር ግን ወንድ ልጅ ከሆነ ጥቁሩን በግ አርደህ ደሙን ጦር ሜዳ ድረስ ይዘህልኝ ና፡፡” አለው፡፡
ይህንንም ያደርግ ዘንድ ልጁን ቃል አስገብቶ ወደ ጦር ሜዳ ሄደ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እናትየው ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ልጁ ታዲያ ህፃን እህቱን ወዲያው ስለወደዳት ሊገድላት አልፈለገም፡፡ ስለዚህ ጥቁሩን በግ አርዶ ደሙን ወደ ጦር ሜዳ ይዞ በመሄድ እናቱ ወንድ ልጅ እንደወለደች ለአባቱ ዋሽቶ ነገረው፡፡
ከዚያም ተመልሶ ከእናቱና ከእህቱ ጋር አብረው ሲኖሩ አባታቸው በጦር ሜዳ ለብዙ አመታት ቆየ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ የአባትየው መመለሻ መድረሱን ልጁ በሰማ ጊዜ ወደ እህቱ ሄዶ እንዲህ ብሎ አስጠነቀቃት “ተጠንቀቂ! አባታችን ሲመለስ የእሱ ልጅ መሆንሽን ማወቅ የለበትም፡፡ ስለዚህ አባዬ ወይም አባቴ ብለሽ በመጥራት የልጅነት ፍቅርሽን ከማሳየት ይልቅ ልጁ እንዳትመስይው እንደ ሌሎቹ የመንደሩ ልጆች አባባ ብለሽ ብቻ ጥሪው፡፡”
አባትየውም ሲመለስ ልጁ አባዬ ብሎ ሰላምታ ከሰጠው በኋላ ወደ ጎጆው ተመልሶ እህቱን በቅሎ ላይ በመጫን ህይወቷን ለማትረፍ ይዟት ጠፋ፡፡
ከዚያም ብዙ አስማተኞች ወደሚኖሩበት ጫካ ሄደው መኖር ጀመሩ፡፡ ወንድምየውም ብዙዎቹን አስማተኞች ቢገድላቸውም የተወሰኑት ቀርተው ነበር፡፡ በጫካው ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሲኖሩ ከአስማተኞቹ አንድ ወደቤታቸው ይመጣ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ከእህቱ ጋር በመግባባት “አግቢኝ” ብሎ ጠየቃት፡፡
እሷም “ይህማ በባህላችን እንደማይፈቀድ ታውቃለህ፡፡ ስለዚህ ወንድሜን ነው መጠየቅ ያለብህ፡፡” አለችው፡፡
ነገር ግን ማንም ሰው እህቱንም ሆነ ወንድሙን ለአስማተኛ መዳር እንደማይፈልግ አስማተኛው ያውቅ ነበር፡፡
ስለዚህ አስማተኛው ወደ ልጆቹ ቤት ተመላልሶ በመምጣት “ወንድምሽ በፍፁም እንዳገባሽ እንደማይፈቅድ ታውቂያለሽ፡፡ ስለዚህ ወንድምሽን ገድለን እኛ እንጋባ፡፡” እያለ ይወተውታት ጀመር፡፡
በመጨረሻ በሃሳቡ ተስማምታ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠየቀችው፡፡ እሱም የታመመች መስላ እንድትተኛና ከህመሟ ትድን ዘንድ የአስማተኛ ምግብ እንደሚያስፈልጋት ለወንድሟ እንድትነግረው ነገራት፡፡ ከዚያም በኋላ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ይወያያሉ፡፡
ወንድሟም ወደቤት በተመለሰ ጊዜ እህቱ ታማ ስላገኛት ምን ማድረግ እንዳለበት ሲጠይቃት መፍትሔው የአስማተኛ ምግብ ብቻ መሆኑን ነገረችው፡፡ በዚህ ጊዜ ተነስቶ አስማተኛ ፍለጋ ሲሄድ በመንገዱ ላይ ሌላ አስማተኛ አገኘ፡፡ ሌላውም አስማተኛ ማንም ሰው የአስማተኛ ምግብ ቢጠይቀው ክፉ ነገር እንዳለበት ሊያውቅ እንደሚያስፈልገውና ምናልባትም እሱን ሊገድሉት እንደሚችሉ ነገረው፡፡
እናም አስማተኛው “ቢገድሉህም እንኳን አስከሬንህን በበቅሎ ጀርባ ላይ አስረው ወደ ገብስ ማሳ እንዲወስዱት ጠይቃቸው፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ የእህቱ ወዳጅ የሆነው አስማተኛ ወደ እህቱ ሄዶ ምን ማድረግ እንዳለባት ነገራት፡፡ ወንድምየው ወደ ቤት በተመለሰ ጊዜ እህቱ የአስማተኛውን ምግብ በልታ “አሁን ደህና ስለሆንኩ አንድ ጨዋታ እንጫወት፡፡” አለችው፡፡
ወንድምየውም “ምን አይነት ጨዋታ ነው የምንጫወተው?” ብሎ ጠየቃት፡፡ እህትየውም “በቅድሚያ ምሰሶው ላይ እሰረኝ ከዚያ ደግሞ ያንተ ተራ ይሆናል፡፡ አለችው፡፡
የእርሱ ተራ በደረሰም ጊዜ ምሰሶው ላይ ካሰረችው በኋላ አስማተኛውን ጠርታ “ይኸውልህ፣ አሁን ልትገድለው ትችላለህ፡፡” አለችው፡፡
ወንድምየውም “በቅድሚያ ከሞትኩ በኋላ በቅሎ ጀርባ ላይ እንደምታስሩኝና በቅሎውን ወደ ገብሱ ማሳ እንደምትለቁት ቃል ግቡልኝ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም አንዴ ከሞተ በኋላ ምንም ማድረግ አይችልም በማለት ከገደሉት በኋላ በበቅሎ ጀርባ ላይ አስረውት ጠመንጃውንም አብረው በመጫን በቅሎውን ለቀቁት፡፡
በዚህ ጊዜ ሌላኛው አስማተኛ በቅሎውን፣ አስከሬኑንና ጠመንጃውን ከገብሱ ማሳ ውስጥ ስላያቸው ሁሉንም ወደ ቤቱ በመውሰድ አስከሬኑን ካስተካከለ በኋላ የወንድምየው አስከሬን ላይ ትንፋሹን ሲተነፍስበት ወንድሙ ህይወት ዘራ፡፡
ጠመንጃውንም ለወንድምየው ከሰጠው በኋላ “በል፣አሁን አድኜሃለሁ፡፡” አለው፡፡
ወንድምየውም ጠመንጃውን ወስዶ የእህቱ ወዳጅ የሆነውን አስማተኛ ከገደለው በኋላ እህቱን በበቅሎ ጭኖ ወደ ወላጆቻቸው መንደር ይዞ ሄዶ “ይህች እህቴ ናት፤ እኔ የእርሷን ነፍስ ሳድን እሷ ግን ገደለችኝ፡፡” አለ፡፡
ይህ የሚያሳየው መልካም ነገር ለሌሎች ብታደርጉም በምላሹ ክፉ ነገር ሊደረግባችሁ እንደሚችል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|