ፍልፈልና ነብር
በአብዱልቃዲር ጉራቻ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ ፍልፈልና አንድ ነብር የፍየል መንጋ ነበራቸው፡፡ ፍየሎቹንም በተለያዩ ቀናት በየተራ ወደ ግጦሽ ያሰማሩ ነበር፡፡ እናም ፍልፈሉ ባሰማራቸው ቀናት ሁሉ ፍየሎቹ ጠግበው ይመለሱ ነበር፡፡ ነብሩ በሚያሰማራቸው ቀናት ግን ፍየሎቹ በሙሉ በጣም ተርበው ይመለሱ ነበር፡፡
የዚህም ምስጢር ፍልፈሉ በሚጠብቃቸው ቀናት እናቱ ዛፍ ላይ ወጥታ ቅጠሎችን እየቀነጠሰች ለፍየሎቹ እንድትጥልላቸው ስለሚያደርግ ፍየሎቹ እሱን በልተው ይጠግባሉ፡፡ በነብሩ ተራ እለት ግን ፍየሎቹ ከመሬት ከሚግጡት ቅንጥብጣቢ ሳር በስተቀር ሌላ ስለማይበሉ በጣም ተርበው ይመለሱ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ነብሩ “እኔ ስጠብቃቸው ተርበው የሚመለሱት አንተ ግን ስትጠብቃቸው ጠግበው የሚመለሱት ለምንድነው?” ብሎ ፍልፈሉን ጠየቀው፡፡
ፍልፈሉም “እሱማ እኔ በጣም ብልህ ስለሆንኩ ነው፡፡ ምልክት ማድረጊያውን ብረት ጭራቸው ላይ ስላማስርባቸው እሱን ሲያዩ የሚቃጠሉ መስሏቸው በመበርገግ የሚበሉትን ነገር ፍለጋ ወደተለያየ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ አንተ ግን ስታሰማራቸው አንድ ቦታ ስለሚቆሙ ተርበው ይመለሳሉ፡፡” አለው፡፡
ሆኖም ነብሩ በዚህ ውሸት ስላልተታለለ ፍልፈሉ የሚያደርገውን ነገር ቀስ ብሎ መሰለል ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ቀን ተከትሎት ሲሄድ በሩቅ አንዲት ሌላ ፍልፈል ለፍየሎቹ ከዛፍ ላይ ቅጠል ስትወረውርላቸው አየ፡፡ ፍልፈሉም ሊያታልለው በመሞከሩ በጣም ስለተናደደ በሚቀጥለው ቀን ነብሩ ፍየሎቹን ሲያሰማራ ከዛፍ ስር ተደብቆ ዛፉ ላይ በመውጣት የፍልፈሉን እናት ገደላት፡፡
በሚቀጥለውም ቀን ፍልፈሉ ፍየሎቹን ሲያሰማራ እናቱን ቢጣራ፣ ቢጣራ መልስ ስላላገኘ መገደሏን አውቆ ሙሉ ቀን ሲያለቅስ ዋለ፡፡ በጣም ሲያለቅስ በመዋሉም አይኖቹ በጣም ቀልተው ነበር፡፡
የዚያን ዕለት ምሽት ፍልፈሉ ወደቤት ሲመለስ ነብሩ “አይኖችህ ለምንድነው እንደዚህ የቀሉት?” ብሎ ሲጠይቀው ፍልፈሉም “ዛሬ አይን ውስጥ የሚጨመር ጀግና፣ ጎበዝና ደፋር የሚደርግ መድኃኒት አገኘሁ፡፡” አለው፡፡
ነብሩ እርሱም ጀግናና ደፋር መሆን ስለሚፈልግ ለእርሱም ለምን እንዳላመጣለት ጠየቀው፡፡
ፍልፈሉም “እሺ፣ ነገር ግን አንዳንድ ቅደመ ጉዳዮች አሉ፡፡ በቅድሚያ መድኃኒቱን አይንህ ውስጥ ስጨምር ብዙ እንባ ይኖርሃል፡፡ ነገር ግን ይህ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚያ ድምፅ ልትሰማ ትችላለህ፡፡ በዚህም አትሸበር ምክንያቱም ልጆቻችን አብረው ሲጫወቱ ወይም ጡት ሲጠቡ ሊሆን ይችላል፡፡” አለው፡፡
ነብሩም “እሺ” ብሎ በጀርባው በመጋደም አይኖቹን ሲከፍት ፍልፈሉ እጅግ የጋሉ ድንጋዮችን የነብሩ አይኖች ውስጥ ሲጨምርበት አይኖቹ ፈነዳድተው ታወረ፡፡
በዚህ ጊዜ ነብሩ ፍልፈሉን ተጣርቶ “ድንጋዮቹን ከአይኔ አውጥተህ ብርኔን መልስልኝ፡፡” ሲለው ፍልፈሉም “እናቴን ስትመልስልኝ እኔም ብርሃንህን እመልስልሃለሁ፡፡” አለው ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|