አባትን መግደል እራስን መበደል
በኡቱራ ቦሩ የተተረከ
በአንድ ወቅት አስር ወንድ ልጆች የነበሩት ሰው ነበር፡፡ ሰውየው ጎበዝ አዳኝ ስለነበረ ልጆቹም እንደርሱ እንዲሆኑ ይመኝ ነበር፡፡
አደን እጅግ የተከበረ ባህል ስለነበር የመንደሩ ሰዎች ሁሉ የሰውየው ቤተሰብ ጎበዝ አዳኞች እንደሆኑ ያውቁ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰውየው አንድ ችግር ነበረበት፡፡ ይኸውም የበኩር ልጁ አዳኝ ካለመሆኑም በላይ ምንም ነገር መግደል የማይችል ስለነበር ይህ ደግሞ የደካማነት ምልክት ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ ስለሆነም አባትየው የበኩር ልጁን አደን ለማሰልጠን በመወሰን አንድ ቀን ይህንኑ ልጁን ብቻ ይዞ ወደ አደን ሄደ፡፡ በወቅቱ ታዲያ አደን አንድ ሳምንትና ከዚያ በላይ ጊዜ ይፈጅ ስለነበረ እንስሳትን እየተከታተለ በመያዝ ልጁ እንዲወጋቸው ወይም እንዲገድላቸው ይነግረው ነበር፡፡ ሆኖም ልጁ “በፍፁም!” ብሎ እምቢ አለው፡፡ ስለሆነም ልጁ ምንም እንስሳት መግደል ባለመቻሉ ተስፋ ስለቆረጠ አዳኙ ሰው ወደ ቤቱ ለመመለስ ወሰነ፡፡ እናም እሱ ራሱ አንድ እንስሳ ገድሎ ከልጁ ጋር ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
ወደቤታቸው በመመለስ ላይ ሳሉም ሰውየው ስለጣለው ግዳይ እያነሳሳ የጀግና ዘፈን ይዘፍን ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ልጁ ቆም አድርጎት “አባቴ ሆይ! አንድ ክፉ ሃሳብ ወደ አእምሮዬ መጥቷልና ልፈፅመው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
አባትየውም “እንደሱማ አይሆንም፡፡ ክፉ ነገር ባደረግክ ጊዜ አንተም ክፉ ትሆናለህ፡፡” አለው፡፡
ይህንንም ካለው በኋላ አባትየው የገደለውን እንስሳ ተሸክሞ የጀግና ዘፈን እየዘፈነ ከልጁ ፊት ፊት መሄዱን ቀጠለ፡፡
በዚህ ጊዜ ልጁ ጦሩን ሰብቆ አባቱን ጀርባው ላይ ከወጋው በኋላ እንስሳውን ተሸክሞ የጀግና ዘፈን ይዘፍን ጀመር፡፡
በሃገሬው ባህል መሰረት አንድ ትልቅ አደን ሲከናወን የመንደሩ ሰው በሙሉ ከቤቱ ወጥቶ ግዳዩን ይመለከታል፡፡ ልጁም ዘፈኑን እየዘፈነ የገደለውን ይዞ ብቅ አለ፡፡
ታዲያ ልጆቹ ሁሉ “አባታችን የታለ?” ሲሉት ልጁም “እኔ እንጃ! በአደኑ ወቅት ወዴት እንደተሰወረ አላውቅም፡፡” ብሎ መለሰላቸው፡፡ እናም አባታቸውን ቢጠብቁት፣ ቢጠብቁት ማንም ሳይመጣ ቀረ፡፡ የበኩር ልጁም በድንገት ሆዱን ስላመመው ሊሞት በተቃረበ ጊዜ ወንድሞቹ በጣም አዘኑ፡፡
እነርሱም “አባታችን በእንስሳ ተገድሎ ይሆናል፡፡ አሁን ደግሞ ወንድማችን ሊሞትብን ነውና ምን ብናደርግ ይሻላል?” ብለው ተጨነቁ፡፡
ከልጆቹ አንዱ ሁልጊዜ ያባቱን ምክር ይሰማ ነበርና “ተመልከቱ፣ አባቴ ሁልጊዜ ስለሶስት ነገሮች ይመክረኝ ነበር፡፡ አንደኛው ቤቴን ከወንዙ አፋፍ ላይ እንዳልሰራ ሲሆን ይኸውም ወንዙ አንድ ቀን የሞላ እንደሆን ጠራርጎ ስለሚወስደው ሁሉንም ነገር እንዳያሳጣኝ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክር ደግሞ ከደፈጣ ጥቃት ወይም በእንስሳት ከሚደርስ ጉዳት እድን ዘንድ የተከለለ ቦታ ላይ እንዳልገኝ ነበር፡፡ ሶስተኛውም ምክር ምንም አይነት ችግር ባጋጠመኝ ጊዜ ወደ አዛውንቶች ሄጄ የእነርሱን ምክር መሻት ነውና አሁንም ወደእነርሱ እንሂድ፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ዓይነት ዘጠኙ ወንድማማቾች የታመመውን ወንድማቸውን ትተው በአቅራቢያቸው ከሚገኙ አንድ አዛውንት ቤት ሄዱ፡፡ አዛውንቱም ሰው ከላሟ ስር ተኝተው ጡቷን ሲጠቡ ስለደረሱ በጣም ተገረሙ፡፡ በዚህም ጊዜ “ይህ ሰው ጃጅቷልና ምንም አይጠቅመንም፡፡ ሚስቱን ወይም ሌላ ሰው ላሚቷን እንዲያልብ ማድረግ ነበረበት እንጂ እንዴት ላሚቷን ይጠባል?” ብለው ወደቤታቸው መመለስ ጀመሩ፡፡
ነገር ግን የአባቱን ምክር ያስታወሰው ልጅ “ይህ ሽማግሌ ሰውም ቢሆን መላ አያጣም፡፡” አለ፡፡
እናም ወደ ሽማግሌው ሰው ተመልሶ ወንድማቸው ለምን እንደታመመ ሲጠይቃቸው እርሳቸውም ቀና ብለው አይተውት “የላም ጡት የሚጠባ ሽማግሌ ምንም ዋጋ እንደሌለው ሁሉ አባቱንም የሚገድል ልጅ እንደዚያው ነውና ሄደህ ይህንኑ ለወንድሞችህ ንገራቸው፡፡” አሉት፡፡
ልጁም ወንድሞቹ ጋ ሮጦ ደርሶባቸው አብረው ወደቤት ተመለሱ፡፡
እነርሱም ሰውየው ምን እንዳለ ሲጠይቁት እርሱም “የላም ጡት የሚጠባ ሽማግሌ ምንም ዋጋ እደሌለው ሁሉ አባቱንም የሚገድል ልጅ እንደዚያው ነው፡፡” አለኝ ብሎ ነገራቸው፡፡
ይህንንም ከሰሙ በኋላ የታመመውም ልጅ አባቱን መግደሉን ተናዞ ራሱም ሞተ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|