አማትየው
በአብዮት ለገሠ የተተረከ
በአንድ ወቅት ባል፣ ሚስትና የባል እናት በአንድ ቤት ውስጥ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡
አንድ ቀን ታዲያ ባልየው ከሄደበት ወደ ቤት ሲመለስ ሚስቱ አላናግር አለችው፡፡ ሰውየውም ተቀምጦ ችግሩ ምን እንደሆነ ሚስቱን ሲጠይቃት እሷም አማቷ በጣም እያስቸገሯት እንደሆነ ነገረችው፡፡ እናቱ በጣም እንደሚጠሏትና ሁልጊዜ እየጨቀጨቁ ኑሮዋን አስቸጋሪ እንዳደረጉባት ነገረችው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ከእናቱ ጋር መኖር ስለማትፈልግ መፍትሔ እንዲፈልግ ጠየቀችው፡፡
ነገር ግን ባልየው ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ስለገባው ምን ማድረግ እንዳለበት ሚስቱን ጠየቃት፡፡ ሚስቱም እናቱን ከገደላት እነርሱ በደስታ እንደሚኖሩ ነገረችው፡፡ ከዚያም ቁጭ ብሎ ሲያስብ እናቱ አሮጊት መሆናቸውንና ከዚህ በኋላ የወደፊት ራዕይም ሆነ ጥቅም የሌላቸው ስለሆነ እርሱ ግን ከሚስቱ ጋር ጥሩ ኑሮ እንደሚኖር ተገነዘበ፡፡
ስለዚህ እናቱ የዚህን ያህል አስቸጋሪ ከሆኑ ገደል ውስጥ ሊወረውራቸው እንደሚገባ በመወሰን ተሸክሞ ወደ ገድል አፋፍ ይዟቸው ሄደ፡፡
ጥቂት ከሄደ በኋላም እናቱ ሊገድላቸው እንደሆነ ስላወቁ “ልጄ ተጠንቀቅ! እኔን ስትወረውር አዳልጦህ እራስህ ልትወድቅ ወይም እኔ ጎትቼህ አብረን ልንወርድ እንችላለን፡፡ ስለዚህ አንተም እንዳትሞት ስትወረውረኝ በአንድ እጅህ ዛፍ ያዝ፡፡” አሉት፡፡
እርሱም ሊገድላቸው እንደሆነ እያወቁ ለእርሱ ህይወት ሲጨነቁ ሲሰማ በጣም ገረመው፡፡ እናም ምክንያቱን ጠየቃቸው፡፡
እርሳቸውም “ይህንን መገንዘብ የምትችለው ልጅ የወለደችና ግንኙነቱን የምታደንቅ እናት ብቻ ስለሆነች አንተም ልጅ እስክትወልድ ድረስ ይህ ሊገባህ አይችልምና ብቻ ተጠንቀቅ፡፡” አሉት፡፡
እናም እናቱን ከትከሻው አውርዷቸው ምን እየተካሄደ እንደሆነ ራሱን መጠየቅ ጀመረ፡፡ ከዚያም እናቱ ከራሳቸው ህይወት አስበልጠው ለእርሱ ህይወት የሚጨነቁ ከሆነ በጣም ጥሩ ሰው እንደሆኑና የችግሩ ምንጭ ሚስቱ እንደሆነች ተገነዘበ፡፡
በመጨረሻም እናቱን ወደ ቤት ወስዶ ሚስቱን በማባረር ከእናቱ ጋር በደስታ መኖር ጀመረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|