እውነትን ተናግሮ መሞት
በዱለች ሊበን የተተረከ
በአንድ ወቅት አብረው የሚኖሩ አንበሳ፣ ጅብና ቀበሮ ነበሩ፡፡ እነርሱም ከብቶቻቸውን በየተራ ወደ ግጦሸ ያሰማሩ ነበር፡፡
አንድ ቀን ከብቶቹን ማሰማራት የአንበሳውና የቀበሮው ተራ ሲሆን ጅቡ በዚያን ዕለት የእርሱ ላም እንደምትወልድ እርግጠኛ ነበር፡፡ ስለዚህ አንበሳውና ቀበሮው ልዩ እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸው ነገራቸው፡፡
ታዲያ አንበሳው ቀበሮውን ግማሹን ከብቶች ወደ አንድ መስክ እንዲወስዳቸው ካዘዘው በኋላ ግማሹን ደግሞ የጅቡን ላም ጨምሮ ወደ ሌላ መስክ ይዟቸው ሄደ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የጅቡ ላም ወለደች፡፡ አንበሳውም ወዲያው የአንድ ድኩላ ግልገል ወስዶ ከላሟ ስር በማኖር የላሟን ጥጃ ደግሞ ከራሱ በሬ ስር አኖረው፡፡
ቀበሮው ሲመጣ አንበሳው እንዲህ አለው፡፡ “አይገርምም! የጅቡ ላም የድኩላ ግልገል ስትወልድ የእኔ በሬ ደግሞ ጥጃ ወለደ፡፡” ምሽትም ሲሆን ከብቶቻቸውን ይዘው ሲመለሱ የሆነውን ነገር ለጅቡ በነገሩት ጊዜ ጅቡ ደስተኛ ስላልነበረ “ይህ ጥሩ አይደለም፡፡ ጥጃው የላሜ ስለሆነ ወደ መንደሩ አዛውንቶች ሄደን ጥጃው የማን እንደሆነ ልንጠይቃቸው ይገባል፡፡” አለ፡፡
ስለዚህ በሚቀጥለው ቀን አዛውንቶቹ በተሰበሰቡበት ሶስቱም እንስሳት ጥጃው የማን መሆን እንዳለበት የሚያረጋግጡበትን ማስረጃ በየተራ አቀረቡ፡፡
በቅድሚያ ሃሳቡን የማቅረብ ተራው የቀበሮው ነበር፡፡ እርሱም “ሁላችንም ከተወለድን በኋላ ስለማንነታችን የምናውቀው ካደግን በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ እንዴት እንደተወለድንና ማን እንደወለደን ምስክርነት መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡” አለ፡፡
ቀጥሎ ሃሳቡን ያቀረበው አንበሳም እንዲህ አለ “መቼም የአምላክ ስራ ልዩ ነው፡፡ ስለዚህ የአምላክን ስራ ከምንጠራጠር እርሱ የሰጠንን ዝም ብለን መቀበል ነው ያለብን፡፡”
በመጨረሻም የጅቡ ተራ በደረሰ ጊዜ ጅቡ “እንግዲያው አንድ የዱር ፍትህ አለ፡፡ በዚህም ህግ መሰረት ግማሾቹ እናቶች በሹካ ሲበሉ ሌሎቹ መራብ የለባቸውም፡፡” አለ፡፡
ከዚያም አዛውንቱ እርስ በርስ ከተወያዩ በኋላ ፍርዱን ፍልፈሏ እንድትሰጥ ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ፍልፈሏ ስላልተገኘች ሁሉንም እንስሳት እንደገና ሰበሰቧቸው፡፡
እናም በሚቀጥለው ጊዜ ሁሉም እንስሳት ምስክርነታቸውን እንደገና እንዲሰጡ ተጠየቁ፡፡
ቀበሮው “ማናችንም ዘለዓለማዊ አይደለንም፡፡ ሁሉም ትውልድ በመጨረሻ ይሞታል፡፡” አለ፡፡
ከዚያም የአንበሳው ተራ ደርሶ አንበሳው “ዕድል የህይወታችን ትልቁ አካል ስለሆነ ካለ ዕድል መኖር አንችልም፡፡” አለ፡፡
ሶስተኛው ተናጋሪ ጅብ ነበርና እርሱም እንዲህ አለ “ደስተኛ ሰው ሳይኮረኮር ይስቃል፡፡” አለ፡፡
ነገር ግን አሁንም ፍልፈሏ ስላልተገኘች ውሳኔው ለሌላ ጊዜ ተላለፈ፡፡
በመጨረሻም ቀን ፍልፈሏ በስብሰባው ላይ ተገኘች፡፡ ታዲያ ሁሉም ተበሳጭተውባት ስለነበር “ባለፈው ስብሰባ ላይ ለምን አልተገኘሽም? እንደዚህ ያሉ ቦታዎች ላይ የመገኘት ኃላፊነት አለብሽ፡፡” አሏት፡፡
ፍልፈሏም “በመጀመሪያው ቀን ሁለት ተራራዎች ተጣልተው እነርሱን ሳስታርቅ ቆየሁ፡፡ በሁለተኛው ቀን ደግሞ ያረጁትን ደረቅ ዛፎች ከአዳዲሶቹ ቁጥቋጦዎች ስለይ ዋልኩ፡፡ በሶስተኛውም ቀን ምንጩ ተቃጥሎ እሱን ሳጠፋ ዋልኩ፡፡” አለች፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው በጣም ተበሳጭቶ “ምንጩ መች ተቃጠለ? እገድልሻለሁ፡፡” ብሎ አፈጠጠባት፡፡
ፍልፈሏም “ተመልከት! ዛሬ እየዘነበ ነው፡፡ ወደ ግራና ወደ ቀኝ ተመልከት፤ ይህንን ሁሉ ዝናብ ማን ይጠጣዋል” አለችው፡፡
አንበሳውም ግራና ቀኙን ሲመለከት ፍልፈሏ ወደ ቆፈረችው ጉድጓድ እየገባች ሳለ “ከምዋሽ ይልቅ እውነቱን ተናግሬ ብሞት ይሻለኛል፡፡ እናም ጥጃውን የወለደችው ላሟ ናት፡፡” ብላ በመጮህ ወደ ጉድጓዷ ዘላ ገባች፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|