የአባትየው ውርስ
በለሙ ዋጪሌ የተተረከ
በአንድ ወቅት ከሚስቱና ከሁለት ወንድ ልጆቹ ጋር የሚኖር ጠንካራ ገበሬ ነበር፡፡ በጣም ጎበዝ ሠራተኛም ስለነበረ በጣም ሃብታም ነበር፡፡ ነገር ግን ልጆቹ ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ ይፈልግ ስለነበረ እርሱና ሚስቱ እንጂ እነርሱ ምንም ስራ እንዲሰሩ አይፈልግም ነበር፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሚስቱ ስትሞት ልጆቹ ምንም ስራ እንዲሰሩ ስለማይፈልግ የመስኩን ስራም ሆነ የቤቱን ውስጥ ስራ በሙሉ እራሱ ይሰራ ነበር፡፡ ነገር ግን ጊዜ እየገፋ ሲሄድ ስላረጀና ጤናውም እየታወከ ስለሄደ እሱ ሲሞት ልጆቹ ራሳቸውን ማስተዳደር እንደማይችሉ ስለገባው በዚህ ይጨነቅ ጀመር፡፡
እናም ስለዚህ ጉዳይ ለብዙ ጊዜ ሲያስብበት ከቆየ በኋላ ልጆቹን ጠርቶ “እንግዲህ ለእናንተ የማወርሳችሁ ብዙ ወርቅ አለ፡፡ ወርቄንም በሙሉ በመስኩ ውስጥ ስለቀበርኩት መስኩን ቆፍራችሁ ወርቁን ማውጣት የእናንተ ፋንታ ነው፡፡” አላቸው፡፡
ጎረቤቶቹንም ጠርቶ “እኔ የምሞትበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፡፡ ሆኖም ልጆቼ ራሳቸውን ማስተዳደር አይችሉምና እባካችሁ ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ምግባቸውን በማብሰል ተንከባከቧቸው፡፡” ብሎ ተማፀናቸው፡፡
እናም ጎረቤቶቻቸው ለተወሰነ ጊዜ ምግብ ሰጧቸው፡፡
ወንድማማቾቹም ወርቁ እንዲዘረፍባቸው ስላልፈለጉ ጉዳዩን ለማንም ሰው ሳይነግሩ ቁፋሮውን በራሳቸው ተያያዙት፡፡ በዚህ አይነት ማሳውን አንድ በአንድ ቢቆፍሩም ምንም ወርቅ አጡ፡፡
በዚህ ጊዜ ወንድማማቾቹ ቁጭ ብለው ሲያስቡ አንደኛው “አባታችን ያታለለን ይመስልሃል?” ብሎ ሌላኛውን ጠየቀው፡፡
ሆኖም ሌላኛው ወንድም “አይደለም፣ አባታችን ሊያስተምረን የፈለገው ግብርና ወርቃማ ሙያ መሆኑን ይመስለኛል፡፡ ሁሉንም ማሳዎች ብንቆፍርና ብናርሳቸው ሃብታም እንሆናለን፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
እናም እንደሌሎቹ ገበሬዎች ማሳዎቹን ሁሉ አርሰው ስንዴ በመዝራት በጣም ሃብታም ሆኑ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|