ሁለት ቀናተኛ ሚስቶች
በቆንጂት ተፈራ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሁለት ሚስቶች የነበሩት ሰው ነበር፡፡ አንደኛይቱ መሃን ስትሆን ሌላኛዋ ግን መሃን አልነበረችም፡፡ ባልየውም ቤት ባልነበረበት ጊዜ አንደኛዋ ሚስቱ መንታ ልጆች ወለደች፡፡ መሃኗ ሚስት ግን በጣም ስለቀናች ትንሽ ደም ወስዳ የአራሷ አፍ ላይ ቀባችው፡፡ መንትዮቹንም ህፃናት ወስዳ ወንዝ ውስጥ ጣለቻቸው፡፡ ባሏም ወደቤት በተመለሰ ጊዜ “ሚስትህ ምን ዓይነት ክፉ እንደሆነች ተመልከት! ውድ ልጆችህን በላቻቸው፡፡” አለችው፡፡
ባልየውም የወላዷን እናት አፍ በተመለከተ ጊዜ አፏ ላይ ደሙን ስላየው ቀናተኛዋን ሚስቱን አመናት፡፡ አራሷን እናት ከገረፋት በኋላ ካለ ምንም ምግብና መጠጥ አህዮች ጋጣ ውስጥ አሰራት፡፡ ስለዚህ የአህዮቹን ፋንዲያና ሽንት መመገብ ጀመረች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባጋጣሚ ዋናተኞች የሆኑ ሰዎች መንትዮቹ ወደ ወንዙ ሲጣሉ ስላዩ ልጆቹን ወስደው አሳደጓቸው፡፡
የሚኖሩበት ትንሽ መንደር በመሆኑ ወሬው ተሰማ፡፡ ሰውየው እናትየውን ወስዶ በአህዮች ጋጣ ውስጥ እንዳሰራትም ታወቀ፡፡
እናም መንትዮቹ ሲያድጉ የማደጎ ልጆች መሆናቸውንና እናታቸው በአህዮች ጋጣ ውስጥ እንደምትኖር እንዲሁም አባታቸው ከመሀኗ ሚስቱ ጋር እንደሚኖር ተነገራቸው፡፡ ስለዚህ ልጆቹ በቀል አርግዘው አደጉ፡፡
ከዚያ በኋላም ወደ ወላጆቻቸው ቤት ሄደው እናታቸውን ወስደው ካጠቧት በኋላ እንደሚንከባከቧት ነገሯት፡፡
አባታቸውንም “ከአንተ ጋር ምንም ማድረግ አንፈልግም! ነገሮችን በትክክል መፍረድ ስላልቻልክ ከእንግዲህ ልናይህ እንኳን አንፈልግም፡፡” አሉት፡፡
መሃኗንም ሚስት ለመቅጣት ፈልገው ወደ መንደሩ አዛውንቶች ወስደዋት “የእርሷ ወንጀል እኛ ላይ የመግደል ሙከራ ማድረጓና በሁለተኛዋ ሚስት ላይ ይህንን ሁሉ በደል ማድረሷ ነው፡፡” ብለው ከሰሷት፡፡
በዚህም የሞት ፍርድ እንዲወሰንባት ተስማሙ፡፡ በዚህ አገር ህግ መሰረትም የሞት ፍርድ የሚፈፀመው የተፈረደበት ሰው በህይወቱ ተቀብሮ ከብቶች በላዩ ላይ በመንዳት ነው፡፡
እናም ቀናተኛይቱ ሚስት በዚህ ዘግናኝ አኳኋን ተገደለች፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|