ሰውና እንስሳቱ
በመሬም መሃመድ የተተረከ
ሰው፣ አንበሳ፣ አህያ፣መርዛማ እባብና ጭልፊት አሞራ በአንድነት ሆነው ወደ ጦርነት ሲሄዱ ብዙ ቀናትን በጉዞ ላይ አሳለፉ፡፡ በጎዞአቸውም ላይ አንድ ቀን ሲመሽ የሚተኙበትን ቦታ ፈለጉ፡፡ ዙሪያቸውንም ሲቃኙ አንዲት ጭስ የሚወጣባት ጎጆ አዩ፡፡ የጭሱንም አቅጣጫ በመከተል ወደ ሰውየው ቤት ሄዱ፡፡ በባህሉ መሠረት መንገደኞቹ ለማደር ጠየቁ፡፡
ነገር ግን ባልና ሚስቱ “እንግዶቻችንን የምናበላቸው ምግብ የለንምና ምን እናድርግ?” ተባባሉ፡፡
አንዲት ላም ነበረቻቸውና ላሟን ሊያርዱላቸው አስበው ይህንን ካደረጉ ግን ምንም ነገር አይቀራቸውም፡፡
ስለዚህ ከእንግዶቻቸው ጋር ተወያይተው እንዲህ አሉ፡፡ “አንዲት ላም አለችን፡፡ ነገር ግን ያለችን እሷው ብቻ ስለሆነች አሁን እሷን ከሰጠናችሁ ወደፊት እንድትከፍሉን እንፈልጋለን፡፡ መብላት የምትፈልጉትንና በምትኩ ምን እንደምታደርጉልን ንገሩን፡፡” አሏቸው፡፡
በዚህ ጊዜ አንበሳው “የላሚቷን ደም ብጠጣና ትንሽ ስጋዋን ከበላሁ ወደፊት ልከፍላችሁ ቃል እገባለሁ፡፡” አላቸው፡፡
ውሻውም “አጥንቶች ካገኘሁ አንድ ቀን እከፍላችኋለሁ፡፡” አለ፡፡
ሰውም እኔ የምፈልገው “ወተቷን ሲሆን አንድ ቀን ልከፍላችሁ እኔም ቃል እገባለሁ፡፡” አለ፡፡
መርዛማውም እባብ “እኔ የምፈለገው ቆንጆ ሞራ ሲሆን ውለታችሁንም ከጥቂት አመታት በኋላ እከፍላችኋለሁ፡፡” አለ፡፡
አህያውም “እኔ እንኳን ላሟን ሳይሆን ትንሽ ጥሩ ሳር ከጎጇችሁ ጣሪያ ላይ ብትሰጡኝ ውለታችሁን እከፍላለሁ፡፡” አለ፡፡
ጭልፊቷም “መቼም ቆዳው ላይ የተራረፈ ፍቅፋቂ ሥጋ አይጠፋምና ያንን ከሰጣችሁኝ ውለታውን እከፍላለሁ፡፡” አለች፡፡
ከዚያ በኋላ ሰውየውና ሚስቱ ላሚቷን ካረዱ በኋላ ደሟን ለአንበሳው፣ አጥንቷን ለውሻው፣ ሞራዋን ለእባቡ፣ የቆዳዋን ሥጋ ለጭልፊቱ ከሰጧቸው በኋላ ለአህያው ትንሽ ሣር ከጣሪያው ላይ አውርደው ሰጡት፡፡
ከዚያም በማግስቱ እንግዶቹ እንስሳት መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡
አንበሳው ባልና ሚስቱን “አንድ ቀን አገሳለሁ፡፡ ሳገሳ ስትሰሙኝም ከጎጇችሁ ወጥታችሁ ምን እንደምሰጣችሁ ታዩኛላችሁ፡፡” ብሏቸው ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን በጠዋት አንበሳው አገሳ፡፡ ሰውየውም ከጎጆው ሲወጣ አንድ ግዙፍ የዝሆን ጥርስ አገኘ፡፡ በዚህም በጣም ተደስቶ ጥርሱን ይዞ ወደቤት ገባ፡፡ ከዚያም በአካባቢው በሙሉ ምንም አይነት ሌባ እንደማይኖርና ውሻው እንደሚጠብቀው አስተውሎ በጣም ደስ አለው፡፡
ከሰባት አመታት በኋላ በጣም መጥፎ ሰው የነበረው የሰውየው ታናሽ ወንድም ሃብታም ሆነ፡፡ ስለዚህ መርዛማው እባብ ነክሶ ወንዱሙን ገደለው፡፡ በሃገሩም ባህል መሠረት ሰውየው የታናሽ ወንዱሙን ንብረት በሙሉ ስለወረሰ በጣም ተደሰተ፡፡
ከዚያም አንድ ቀን ጭልፊቷ አዛውንቶች የተጣሉ ባልና ሚስት ለማስታረቅ ብዙ ስጦታ ይዘው ሲሄዱ ታያቸዋለች፡፡ በዚህ ጊዜ ጭልፊቷ ዥው ብላ ወርዳ ውድ ስጦታዎቹን ከአዛውንቶቹ ላይ በመንጠቅ ሰውየው እንዲጠቀምባቸው ወሰደችለት፡፡
ውለታቸውን ሳይከፍሉ የቀሩት አህያዋና ሰውየው ብቻ ነበሩ፡፡
ታዲያ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አህያውን ብር እየጫኑ በማመላለሻነት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ አህያው በጫካው ውስጥ እየተጓዘ ሳለ ድንገት አምልጦ የተጫነውን የብር ማዕድን በሙሉ ይዞ ወደ ሰውየው ቤት ሄደ፡፡
በሚገርም ሁኔታ ሰውየው ብቻ የገባውን ቃል ሳያከብር በዚያው ጠፍቶ ቀረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|