የንጉሱ አይጥ ልጅ
በመርጋ ደበሎ የተተረከ
ይህ ታሪክ ስለ አይጦች የሚተርክ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ራሳቸውን በምድር ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ በላይ አድርገው የሚቆጥሩ የአይጥ መንጋ አባላት ነበሩ፡፡ አይጦቹም በጣም ትምክህተኞችና ህልመኞች የነበሩ ሲሆን ራሱን ከእነርሱ በላይ አድርጎ የሚመለከት አንድ ከሁሉም መጥፎ ንጉስ ነበራቸው፡፡
ከጊዜ በኋላ ንጉሱ አይጥ ልጅ ወልዶ “ተመልከቱ! ልጄ በምድር ላይ ካሉ ፍጡራን ሁሉ የላቀ ፍጡር ስለሆነ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሚስት እንዲኖረው እፈልጋለሁ፡፡” አለ፡፡
ነገር ግን እዚህ ምድር ላይ ካሉት የማይረቡ እንስሳት አንዷም ለሚስትነት ስለማትመጥነው የፈጣሪውን ልጅ እንዲያገባ ወሰነ፡፡
ስለዚህ የአገር ሽማግሌዎችን ሰብስቦ “ሄዳችሁ ፈጣሪያችን ልጁን እንዲድርልን ጠይቁት፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም ወደ ፈጣሪ ሄደው “እጅግ በጣም ግሩም ልጅ አለን፤ ቆንጆ ጎበዝና የተለየ ነው፡፡ እናም ሴት ልጅህ ለልጃችን ሚስት ትሆነው ዘንድ እነድትሰጠን እንፈልጋለን፡፡” አሉት፡፡
ፈጣሪም “ከምትናገሩት ነገር በመነሳት ልጃችሁ ምን ያህል ልዩ እንደሆነ ማወቅ ችያለሁ፡፡ እንዲያውም ልጁ እጅግ በጣም ልዩ ስለሆነ ከእኔ ልጅ የተሻለች ማግባት ያለበት ይመስለኛል፡፡” አላቸው፡፡
የአገር ሽማግሌዎቹ ግን “ተመልከት፣ አንተ ከፍጥረታት ሁሉ የላቅህ እንደሆንክ እናውቃለን፡፡” አሉት፡፡
ፈጣሪም እንዲህ አላቸው “አይሆንም፣ እኔ ሰማይ ላይ የምኖር አምላክ ነኝ፤ ጭጋግ መጥቶ ሲሸፍነኝ እንኳን ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ስለዚህ ሄዳችሁ የጭጋጉን ልጅ ጠይቁ፣ በጣም ቆንጆ ናት፡፡”
ሽማግሌዎቹም ወደ ንጉሱ ሄደው “ተመልከት፣ ፈጣሪ ጭጋግ ከእኔ ይበልጣል ካለ ትክክል መሆን አለበት፡፡” አሉት፡፡
ንጉሱም ሽማግሌዎቹ ወደ ጭጋጉ ሄደው ልጁን ለጋብቻ እንዲጠይቁ ላካቸው፡፡
እናም ሽማግሌዎቹ ወደ ጭጋጉ ቤተ መንግስት ሄደው “ተመልከት እኛ ከሁሉ የላቀ ሃያል ልጅ አለን፡፡ አንተም ቆንጆ ሴት ልጅ እንዳለህ ሰምተናልና ልናጋባቸው እንችላለን?” ብለው ጠየቁት፡፡
“ጭጋጉም እስኪ ስለ ልጁ አጫውቱኝ” አላቸው፡፡
ሽማግሌዎቹም “ልጃችን ቆንጆ፣ ጎበዝና ታላቅ ነው፡፡” አሉት፡፡ “ጭጋጉም እንደዚያማ ከሆነ ልጃችን ከእርሱ ስለምታንስ ከእርሷ የበለጠችዋን ነው ማግባት ያለበት፡፡” አላቸው፡፡
ሽማግሌዎቹም “ከጭጋግ የበለጠ ማን አለ? አምላክ እንኳን አንተ እንደምታፍነው አምኗል፡፡” አሉት፡፡
ጭጋጉም “አሃ! ንፋስ ነዋ! አንዴ የመጣ እንደሆን ብትንትኔን ስለሚያወጣው ከእርሱ ጋር አልስተካከልም፡፡ ሴት ልጅ ስላለው ሄዳችሁ ጠይቁት፡፡” አላቸው፡፡
ከዚያም ንጉሱ ዘንድ ደርሰው ወደ ንፋሱ ሄዱ፡፡
ለንፋሱም ስለ ንጉሱ ልጅ በነገሩት ጊዜ ንፋሱ “እንግዲያው ልጃችሁ ከልጄ በላይ ሃያል ነው፡፡ ከንፋስ የበለጠውን ፍጡር ለምን አትጠይቁም?” አላቸው፡፡
“ከንፋስ የሚበልጠው ማነው? አንተ ጭጋግን እንኳን ትበታትናለህ፡፡” አሉት፡፡
ንፋሱም “ሄዳችሁ ተራራውን ጠይቁት፡፡ እርሱ በጥፊ ብሎ ነው ከላዩ የሚገፈትረኝ፡፡” አላቸው፡፡
በዚህም ተስማምተው ንጉሱን ካማከሩት በኋላ ወደ ተራራው ሄዱ፡፡
ለተራራውም ችግራቸውን በነገሩት ጊዜ ተራራው “ሃሳባችሁ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ልጄ ልጃችሁን ለማግባት አትመጥነውም፡፡ ከእኔ የበለጠ ፍጡር አለ፡፡” አላቸው፡፡
ሽማግሌዎቹም “እሱ ማነው?” አሉት፡፡
ተራራውም “ውስጤን ቦርብሮ የሚፈረካክሰኝ የዱር አይጥ የሚባል እንስሳ አለ፡፡” አላቸው፡፡
ስለዚህ ወደ አይጡ ንጉስ ሄደው “እንግዲህ ተራራው የዱር አይጥ ከእርሱ እንደሚበልጥ ነግሮናል፡፡ ሄደን እሱን እንጠይቀው” ብለው አማከሩት፡፡
ንጉሱም “በጣም ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡ ዘመዳማቾችም ስለሆንን ጥሩ እንግባባለን፡፡” አለ፡፡
የታሪኩ መልዕክትም አንድን ሰው በጥሩ መልኩ ከቦታው ማኖር እንደሚቻል ያሳያል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|