የተረገመች እንጀራ እናት
በመርጋ ደበሎ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሁለት ሴት ልጆች የነበራቸው ባልና ሚስት አብረው በደስታ ይኖሩ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ሚስቲቱ ስትሞት ባልየው ልጆቹን ብቻውን ማሳደግ ቸገረው፡፡ ስለዚህ እንደገና ማግባት እንዳለበት ወስኖ ሚስት የምትሆነውን ሴት መፈለግ ጀመረ፡፡
አንድ ሊያገባት የፈለጋት ሴት “እኔ ማግባት የምፈልገው ልጆች የሌሉትና ያላገባ ሰው ነው፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ሰውየው የሚያደርገው ነገር ግራ ስለገባው ሁለቱን ሴት ልጆቹን ቁጥቋጦ ውስጥ ከደበቃቸው በኋላ “ተመልከቺ እዚህ ቁጥቋጦ ውስጥ የሟች አባቴና የቅደመ አያቶቼ ነፍሶች ስላረፉ በቀን ሶስት ጊዜ ማለትም ቁርስ፣ ምሳና እራት እንድትወረውሪላቸው እፈልጋለሁ፡፡” አላት፡፡
እናም በዚህ ዓይነት ምግብ ወደ ቁጥቋጦው እየወረወሩላቸው ለተወሰነ ጊዜ አብረው ኖሩ፡፡
አንድ ቀን ሚስቲቱ ፀጉሯን ለመቆረጥ ወደ ፀጉር ሰሪ ቤት ሄዳ ፀጉር ሰሪዋን “እባክሽ ቶሎ ቶሎ ስሪኝ፤ ለባለቤቴ ቅድመአያቶች ምግብ መስጠት አለብኝ፡፡” አለቻት፡፡
ፀጉር ሰሪዋም “አንቺ አብደሻል እንዴ? ሴት ልጆቹን እኮ ነው ደብቆ አንቺ የምትመግቢያቸው፡፡” አለቻት፡፡
በዚህ ጊዜ የእንጀራ እናቷ በጣም ተበሳጭታ በትልቅ እንስራ ውሃ ካፈላች በኋላ የፈላውን ውሀ ልጆቹ ወዳሉበት ቁጥቋጦ ውስጥ ደፋችው፡፡ ሆኖም ልጆቹ ወደ አንድ በኩል ስለሸሹ ውሃው ያረፈው በሽንብራው ላይ ነበር፡፡ ልጆቹም አባታቸው እስኪመጣ በፈላው ውሃ የተቀቀለውን ሽንብራ እየበሉ ጠበቁት፡፡
ባልየውም ሲመጣ ሚስቱ በጣም በመናደድ “ስማ ሁለቱን ሴት ልጆችህን እንድታስወግድልኝ እፈልጋለሁ፡፡ እነርሱን ማየት አልፈልግም፡፡ ሚስጥርህንም ደርሼበታለሁ፡፡” አለችው፡፡ ትንሽ ስንቅ ካስያዘቻቸው በኋላ አባታቸው ወደ አንድ ግዙፍ ደን ይዟቸው ሄደ፡፡ እዚያም ብዙ ትልልቅ ዛፎች፣ ዝግባና ፅድ የመሳሰሉ ነበሩ፡፡
አባታቸውም “እነዚህ ዛፎች ስር እንተኛ፡፡” ብሎ ከመሃከላቸው ሆኖ አብረው ተኙ፡፡
ልጆቹም እንቅልፍ በያዛቸው ጊዜ አንድ ትልቅ ግንድ በመሃከላቸው በማጋደም እሱ ያለ እንዲመስላቸው በማድረግ እዚያው ያሉበት ትቷቸው ሄደ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ በጣም የራበው ጅብ ወደ እነርሱ መጣ፡፡ ሆኖም እንደ እድል ሆኖ ልጆቹ የለበሱት ከቆዳ የተሰራ ልብስ ስለነበረ ልብሳቸውን ትንሽ በትንሽ እየበጨቁ እስኪነጋ ድረስ ጅቡን ሲመግቡ ቆዩ፡፡
ከሁለቱ አንደኛዋ ልጅ ብልጥ ስትሆን ሌላኛዋ ደደብ ነበረች፡፡ እናም ብልጧ ልጅ አንድ ዛፍ ላይ ወጥታ በሩቅ ስትመለከት የአንድ አስማተኛ ቤት አየች፡፡ አስማተኛው ብዙ ከብቶች የነበሩት ሃብታም ሰው ነበር፡፡ ታዲያ ሰውየው ከብቶቹን ወደ ግጦሽ ሊያሰማራ ሲወጣ ብልጧ ልጅ ቀስ ብላ ወደቤቱ በመግባት ወተትና ምግብ ወስዳ እህቷንም እየመገበች አብረው ዛፍ ላይ መኖር ጀመሩ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ ደደቧ ልጅ “አይሆንም! እኔም ሄጄ መስረቅ አለብኝ፡፡” ብላ ሄደች፡፡
ሆኖም ቀርፋፋና ድንቅፍቅፍ ስለነበረች አስማተኛው ሰው ይዞ ከአንድ ትልቅ ጆንያ ውስጥ ከቶ ካሰራት በኋላ ከጣራው ሥር ባለው ወራጅ ላይ አስሯት ሄደ፡፡ ነገር ግን ብልጧ ልጅ ተደብቃ ይህንን ሁሉ ስታይ ስለቆየች አስማተኛው ሰው ሲሄድ ወደ ቤቱ ገብታ እህቷን ፈታቻት፡፡ ከዚያም ጆንያውን በትልልቅ ድንጋዮች ሞሉት፡፡ አስማተኛው ማታ ወደ ቤቱ ሲመለስ ጆንያውን ወጋግቶ ስለበሳሳው ድንጋዩ ሁሉ እላዩ ላይ ወድቆበት ገደለው፡፡
ልጆቹም በቤቱ ውስጥ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ሆኖም ሁልጊዜ ውሃ ለመቅዳትና ስራ ለመስራት የሚትሄደው ብልጧ ልጅ ነበረች፡፡ በጣም ፈጣንና ቀልጣፋ ነበረች፡፡
አንድ ቀን ደደቧ ልጅ “አሁን የእኔ ተራ ነው፤ ሄጄ ውሃ ማምጣት አለብኝ፡፡” ብላ ወደ ወንዝ በወረደች ጊዜ ሁለት ሰዎች ከወንዙ አፋፍ ላይ አግኝታ እነርሱም “አሁን ወደቤት ሂጂ፤ ታዲያ በመንገድሽ ላይ ሸንበቆ እየጣልሽ ስትሄጂ እኛም እሱን እያየን እንከተልሻለን፡፡” አሏት፡፡
በዚህ አይነት ሁለቱ ሰዎች ተከትለዋት እቤት ድረስ አብረዋት ሄዱ፡፡ አንደኛው ሰው ብልህ ሲሆን ሁለተኛው ግን ደደብ ነበር፡፡ እናም ብልሁ ሰው ብልጧን ልጅ ሲያገባ ደደቡ ሰው ደግሞ ደደቧን ልጅ አገባ፡፡ አብረውም እስከተወሰነ ጊዜ ኖረው ልጆች ወለዱ፡፡
አንድ ቀን ብልጧ ልጅ ከቤት ስትወጣ ደደቧን “ልጄን በሙቅ ውሃ እጠቢልኝ፡፡” አለቻት፡፡
ሆኖም ደደቧ ልጅ ህፃኑን በፈላ ውሃ ውስጥ አስገብታ ገደለችው፡፡ ብልኋም ልጅ እጅግ በጣም ስለተበሳጨት እህቷን ሰድባ “ውጪልኝ! ሂጂ ከዚህ!” አለቻት፡፡
በዚህ ሁኔታ ደደቦቹ ባልና ሚስት ትንሽ ስንቅ ይዘው ከልጆቻቸው ጋር ቤቱን ለቀው ሄዱ፡፡ በመንገዳቸውም ላይ ከአንድ ወንዝ አጠገብ ሲደርሱ ልጅቷ ስንቁን እንደተሸከመች ወንዙን ዘላ ልታቋርጥ ስትሞክር ማዕበሉ ይዟት ሄደ፡፡
ነገር ግን ባሏ ብቻውን ምግቡን ልትበላ የሄደች መስሎት ድንጋይ ሲወረውርባት ጭንቅላቷ ላይ ስለመታት መድማት ጀመረች፡፡
ውሃውም ቀይ በሆነ ጊዜ “ይኸው ምግቡን እየበላች ስለሆነ ሥጋው መንሳፈፍ ጀመረ፡፡” አለ፡፡
ይህንንም ብሎ ወንዙ ውስጥ ዘሎ ገብቶ ሞተ፡፡
ወደሚቀጥለው > |
---|