ርግቧ ታድነኛለች
በኢብራሂም ሸሪፍ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ በጣም ሃብታም ሰው ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ሃብትና ንብረቱን በሙሉ ሰብስቦ ወደ ሌላ ከተማ ሄዶ ለመኖር ጉዞ ጀመረ፡፡ በመንገዱም ላይ አንድ እንግዳ ሰው አግኝቶ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ አብረው መጓዝ ጀመሩ፡፡
እንግዳው ሰው ሰላማዊ መንገደኛ ቢመስልም ከጥቂት ቆይታ በኋላ አንድ ፀጥ ያለ ቦታ ሲደርሱ እንግዳው ሰው ሃብታሙን ሰው “አሁን ልገድልህ ነውና የሚያድንህ ማነው?” አለው፡፡
ሃብታሙም ሰው ግራ ቀኙን ቢያይ ምንም ሰው የለም፤ ቀና ብሎ ሲመለከት አንዲት እርግብ ዛፍ ላይ ተቀምጣ ሲያይ “ይህች እርግብ ታድነኛለች፡፡” አለ፡፡
እንግዳውም ሰው በጣም በመደነቅ ከት ብሎ ከሳቀ በኋላ ሃብታሙን ሰው ገድሎ ንብረቱን በሙሉ ከዘረፈ በኋላ ወደ ከተማው ሄዶ እዚያ መኖር ጀመረ፡፡ በጣም ሃብታም ሰው ስለሆነም ቤተመንግስት ውስጥ ድግስም ሆነ ስብሰባ በተደረገ ጊዜ ተጋብዞ ይሄድ ጀመር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ንጉሱ በጣም ትልቅ ድግስ ደግሶ ህዝቡን ሁሉ እንግዳውንም ሰው ጭምር ጋበዘ፡፡ ግብዣው በብዙ የምግብ አይነቶች የተትረፈረፈ ስለነበረ ሰው ሁሉ የፈለገውን ይመገብ ነበር፡፡ እንግዳውም ሰው የወደደውን ምግብ ይመርጥ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ አንዲት የተጠበሰች ርግብ አየ፡፡ ሃብታሙን ሰው እንዴት እንደገደለው አስታውሶ ሲስቅ ንጉሱ አየውና በእርሱ የሚያሾፍ መስሎት ወታደሮቹ ይዘውት እነዲገድሉት አዘዘ፡፡
በዚህ ጊዜ እንግዳው ሰው መሞቱ ስለማይቀርለት ለምን እነደሳቀ ለመናገር ወሰነ፡፡ ንጉሱም ምክንያቱን ከሰማ በኋላ አስገደለው፡፡ የእንግዳውም ሰው ሃብትና ንብረት በሙሉ ለሃብታሙ ሰው ህጋዊ ወራሾች ተመለሰ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|