አትራሱና አሜጋግ
በኢብራሂም ሸሪፍ የተተረከ
ከብዙ ዘመናት በፊት በሃረር ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ አትራሱ የሚባል ሰው ነበር፡፡ አትራሱ ተንኮለኛና ሌባ ነበር፡፡ በሃረር ከተማ ውስጥ ግን ነዋሪዎቹ ስለሌባነቱ ለማወቅ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ በሄደበት ቦታ ሁሉ ሰዎች ይጠቋቆሙበት ነበር፡፡
ከዚያም “ባህሪዬ በከተማው ሰዎች ሁሉ ዘንድ ስለሚታወቅ ሰው ወደማያውቀኝ ወደ ሌላ ከተማ ብሄድ ይሻለኛል፡፡” ብሎ አሰበ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ አሜጋግ የሚባልና በሌላ ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ ሌባ የሚኖርበትን ከተማ ለቆ ለመሄድ ይወስናል፡፡
ታዲያ አትራሱ አንድ ቅል አዘጋጅቶ በአመድ ከሞላው በኋላ በአናቱ ላይ ትንሽ ማር ጨምሮበት ሊሸጠው ጉዞ ጀመረ፡፡ አሜጋግም ቅሉን በአሸዋ ሞልቶ በአናቱ ላይ ትንሽ ቅቤ በማድረግ ሌላኛው ከተማ ወስዶ ሊሸጠው ጉዞውን ይጀምራል፡፡ በመንገዳቸውም ላይ አንዱ ወደ ሌላኛው ከተማ ሲጓዝ ተገናኝተው ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ አተራሱ ወደ ሌላው ከተማ ሄዶ ማሩን ሊሸጥ እንደሚጓዝ ተናገረ፡፡
አሜጋግም “እኔ ደግሞ ወደ ሌላው ከተማ ሄጄ የያዝኩትን ቅቤ በመሸጥ ማር ልገዛ እየተጓዝኩ ነውና ቅር ካላለህ ብንለዋወጥስ?” አለው፡፡
በዚህም ተስማምተው ቅሎቻቸውን ተቀያየሩ፡፡ ሁለቱም በመጨረሻ አንድ የሚያታልሉት ሰው በማግኘታቸው ተደስተው ወደየመጡበት ተመለሱ፡፡
ቤታቸውም እንደደረሱ ቅሎቻቸውን ሲከፍቱ በሚያስገርም ሁኔታ መታለላቸውን አዩ፡፡ ሁለቱም ሰዎች በጣም በመበሳጨት እቃቸውን ወደተቀያየሩበት ቦታ ለማምራት ወሰኑ፡፡ ከስፍራውም ሲደርሱ ተገናኝተው ወዲያው ሰላም አውርደው ሁለቱም የታወቁ ሌቦች በመሆናቸው አብረው ለመስራት ወሰኑ፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ወደማይታወቁበት ሶስተኛ ከተማ በመሄድ ኑሮ ለመመስረት ወሰኑ፡፡
ከረጅም ጉዞ በኋላ የአንድ ጂኒ ቤት ደርሰው እዚያው ስራ አገኙ፡፡ አትራሱ ላም እንዲጠብቅ ሲመደብ አሜጋግ ደግሞ ግቢውን እንዲያፀዳ ተመደበ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ አትራሱ ላሚቷን ለግጦሽ ወደ መስክ ይዟት ሄዶ ሣለ ላሚቷ በድንገት መሮጥ ጀመረች፡፡ እርሱም ላሚቷን እየተከታተለ ግራና ቀኝ እየተሯሯጠ ሙሉ ቀን ላይ ታች ሲል ውሎ በመጨረሻም ላሚቷ ስትቆም ወደቤት ወሰዳት፡፡
አሜጋግም በበኩሉ ሙሉ ቀን ግቢውን ሲያፀዳ ሲውል መሬቱን በአንድ ወገን ሲጠርግ ከባድ ነፋስ አቧራውን መልሶ ሲያለብሰው እንደገና ሲያፀዳ እንደገና ሲቆሽሽ ውሎ ወደ ማታ ላይ ነፋሱ ሲቆም ፅዳቱን ጨረሰ፡፡
ማታ ተኝተው እያለ አትራሱ “ሥራዬ በጣም ቀላል ነው፡፡ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብዬ ላሚቷ ስትግጥ ማየት ብቻ ነው፡፡” አለ፡፡
አሜጋግም “የእኔ ስራ እንዲያውም ከዚህ ይቀላል፡፡ አንድ ጊዜ ግቢውን ካፀዳሁ ሙሉ ቀን ስጋደም ነው የምውለው፡፡” አለ፡፡
ስለዚህ ስራቸውን ለመቀያየር ወሰኑ፡፡
በሚቀጥለው ቀን አሜጋግ ላሚቷን ሲያሯሩጥ ውሎ ሲመሽ በጣም ደክሞት ወደ ቤት መጣ፡፡ አትራሱም በበኩሉ ሙሉ ቀን ሲጠርግ፣ ሲለቅም እንደገና ሲጠርግ ዋለ፡፡
ማታ ሲገናኙም ሥራው በጣም አድካሚ በመሆኑ ሌላ ስራ ለመፈለግ ተስማሙ፡፡ ከመሄዳቸውም በፊት ጂኒው የሰሩበትን ገንዘብ እንዲከፍላቸው ጠየቁት፡፡
ጂኒውም “ገንዘቡ ቅሉ ውስጥ ስለሆነ እጃችሁን ሰዳችሁ የፈለጋችሁትን ያህል ውሰዱ፡፡” አላቸው፡፡
አትራሱ እጁን ቅሉ ውስጥ ሲከት ጣቶቹ በሙሉ ተቆረጡ፡፡ ሆኖም አሜጋግ እንዳያየው እጁን ቶሎ ብሎ ክንዱ ስር በመደበቅ “እኔ ድርሻዬን ወስጃለሁና አንተም ሄደህ ድርሻህን ውሰድ፡፡” አለው፡፡
አሜጋግም እጁን ቅሉ ውስጥ ሲከት ጣቶቹ ስለተቆረጡ እንዲህ እያለ ይጮህ ጀመር “ጣቶቼ ተቆረጡ! ጣቶቼ ተቆረጡ!” ለአትራሱም እጁን ሲያሳየው አትራሱም የተቆረጡትን ጣቶቹን አሳየው፡፡
ከዚያን ዕለት ጀምሮ ሁለቱ አጭበርባሪ ሌቦች ቀሪ ህይወታቸውን አካለ ጎደሎ ሆነው መኖር ጀመሩ፡፡
< ወደኋላ |
---|