መልካሙ ሰውና ክፉው ሰው
በኢብራሂም ሸሪፍ የተተረከ
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ሰዎች አብረው ይጓዙ ነበር፡፡ ታዲያ አንደኛው ሌላኛውን “ምንም የምበላው ነገር የለኝምና የሚበላ ነገር ካለህ እባክህ ስጠኝ፡፡” አለው፡፡
መልካሙ ሰው በጣም ደግ ስለነበረ የያዘውን ምግብ ተካፍለው እየበሉ ጉዟቸውን አብረው ቀጠሉ፡፡ በጉዟቸውም መሃል ስንቃቸው አለቀ፡፡ ክፉው ሰው ግን የራሱን ስንቅ ደብቆ ስለነበረ የመልካሙ ሰው ስንቅ ሲያልቅ የራሱን አምጥቶ ብቻውን ይበላ ጀመር፡፡
መልካሙም ሰው ይህን ባየ ጊዜ ትንሽ ምግብ ይሰጠው ዘንድ ክፉውን ሰው ለመነው፡፡ ክፉው ሰው ግን በጣም ራስ ወዳድ ስለነበረ “ምግቡን አልሰጥህም፡፡” በማለት ብቻውን መብላቱን ቀጠለ፡፡ መልካሙ ሰው በጣም ስለተራበና ተስፋ ስለቆረጠ ከመሞቱ በፊት ትንሽ ምግብ እንዲሰጠው መማፀኑን ቀጠለ፡፡
ክፉው ሰው ግን “ምግብ ከፈለክ አንድ አይንህን ላውጣና ምግብ እሰጥሃለሁ፡፡ ካለበለዚያ በረሃብ ትሞታለህ፡፡” አለው፡፡
መልካሙም ሰው ሌላ ምርጫ ስላልነበረው አንድ አይኑን እንዲያወጣው ፈቀደለት፡፡
ከተወሰነ ጌዜ በኋላ ደጉ ሰው እንደገና ራበው፡፡ አሁንም ክፉውን ሰው ምግብ ቢጠይቀው አልሰጥህም አለው፡፡
መልካሙ ሰው አሁንም አጥብቆ ቢማፀነው ክፉው ሰው “ሌላኛውን አይንህን ላውጣና፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
ደጉም ሰው በጣም ተርቦ ስለነበረ ክፉው ሰው የቀረውን አይኑን እንዲያወጣ ፈቀደለት፡፡ ክፉውም ሰው አይኑን አውጥቶ ምግብ ሰጠው፡፡
ጉዟቸውንም ቀጠሉ፡፡ ከአንድ ከተማም እንደደረሱ ክፉው ሰው መልካሙን ሰው ከአንድ ዛፍ ስር አስቀምጦት ትቶት ሄደ፡፡ መልካሙም ሰው እስኪመሽ ድረስ እዚያው ዛፍ ሥር ተቀምጦ ዋለ፡፡ ማታ ማታ ታዲያ ይህ ዛፍ የጂኒዎች መሰብሰቢያ ስፍራ ነበር፡፡ በጣም በጨለመ ጊዜ ጂኒዎቹ ዛፍ ስር ተሰባስበው እርስ በርስ መነጋገርና መወያየት ጀመሩ፡፡
ዓይነ ስውሩንም ሰው ባገኙት ጊዜ ከጂኒዎቹ አንዱ “የዚህ ዛፍ ቅጠል ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች እንደገና እንዲያዩ ያደርጋል፡፡” አለ፡፡
ሁለተኛውም ጂኒ “የንጉሱ ሴት ልጅ ሽባ ሆና ምንም አይነት መድሃኒት እስካሁን አልተገኘላትም፡፡ ንጉሱ ግን ጥቁር ውሻ አርዶ በውሻው ደም ቢያጥባት ትድናለች፡፡” አለ፡፡
ሶስተኛውም ጂኒ “የዚህች ከተማ ነዋሪዎች ሙሉ ቀን ውሃ ፍለጋ ይዋትታሉ፡፡ ነገር ግን በከተማው መሃከል ያለውን ዛፍ ቢቆርጡት ውሃ ያገኙ ነበር፡፡” አለ፡፡
መልካሙም ሰው ፀጥ ብሎ ቁጭ ባለበት ይህንን ሁሉ ይሰማ ነበር፡፡ ነግቶ ጂኒዎቹ በሄዱ ጊዜ በዳሰሳ የዛፉን ቅጠሎች ቀንጥሶ አይኑን ሲያሽበት ብርሃኑ ተመለሰ፡፡
ከዚያ በኋላ ወደከተማዋ ሄዶ ሰዎቹ ንጉሱ ዘንድ እንዲያደርሱት ጠየቀ፡፡
ንጉሱም ዘንድ በቀረበ ጊዜ ሠላምታ ከሰጠ በኋላ ልጁን ሊያድናት እንደሚችል ነገረው፡፡
የንጉሡም አማካሪዎች ግን የሚቻለውን ነገር በሙሉ መሞከራቸውንና ሊያድኗት አለመቻላቸውን ገልፀውለት ተጨማሪ ሙከራ ዋጋ እንደሌለው ነገሩት፡፡
መልካሙ ሰው ግን ውትወታውን ስለገፋበት ንጉሱ ተስማማ፡፡ ከዚያም አንድ ጥቁር ውሻ አምጥቶ ከገደለው በኋላ በደሙ ልዕልቷን አጠባት፡፡ ልዕልቲቱም ዳነች፡፡ ንጉሱም በጣም በመደሰት ሽልማት ሰጠው፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ የከተማው ነዋሪዎች ውሃ ፍለጋ ሲንከራተቱ አያቸው፡፡ ለንጉሱም “ጥቂት ሠራተኞን ብትሰጠኝ ለህዝቡ ውሃ አወጣላቸዋለሁ፡፡” አለው፡፡
ሠራተኞችም ተሰጥተውት በከተማው እምብርት ላይ የቆመውን ዛፍ በሰራተኞቹ እገዛ ቆርጦ ጣለው፡፡ በዚህ ጊዜ ውሃ ወጣላቸው፡፡
ንጉሱም በጣም ስለተደሰተ ሴት ልጁን ድሮለት ብዙ ገንዘብ ሰጠው፡፡
አንድ ቀን መልካሙ ሰው ክፉውን ሰው አገኘው፡፡ የሆነውንም ነገር ሁሉ ነገረው፡፡ ተንኮለኛውም ሰው በሁኔታው ተገርሞ “እንዴት እንደዚህ እድለኛ ልትሆን ቻልክ?” አለው፡፡
መልካሙም ሰው ስለጂኒዎቹ ነገረው፡፡
በዚህ ጊዜ ክፉው ሰው “ወደዚያ ዛፍ ሄጄ በማደር ጂኒዎቹ ምን እንደሚሉ መስማት አለብኝ፡፡” ብሎ አሰበ፡፡
እንደተለመደው ጂኒዎቹ መጥተው ስብሰባቸውን ጀመሩ፡፡
አንደኛው ተነስቶ “ስለከተማውና ስለንጉሱ የተነጋገርንባቸው ችግሮች በሙሉ ተፈትተዋል፡፡ ልዕልቲቱም ድናለች፤ ውሃውም እንደልብ እየፈሰሰ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እዚህ ተደብቆ የምንናገረውን ነገር የሚሰማን ሰው አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አድነን እንያዘው፡፡” አለ፡፡ ከዚያም ሲፈልጉ ክፉውን ሰው አግኝተው ገደሉት፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|