ታላቁ ልዑል
በአብዱልራህማን አብዱላሂ የተተረከ
ከብዙ ዘመናት በፊት ሃረር ውስጥ ዓይነ ስውር ንጉስ ነበር፡፡ በጣም ደግና ብልህ ልጅም ነበረው፡፡ ንጉሡ የቻለውን ሁሉ መድሃኒት በመጠቀም ብርሃኑን ለመመለስ ይሞክር ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ትንቢት ተናጋሪ ሰው ወደ ንጉሡ መጥቶ “የንጉሡ ብርሃን ሊመለስ የሚችለው የባህሩን ንጉስ ማለትም ዓሣ ነባሪን ሲያገኘው ብቻ ነው፡፡ የባህሩንም ንጉስ ሊይዝ የሚችለው ሌላ ማንም ሰው ሳይሆን ልጅህ ብቻ ነው፡፡” ብሎ ነገረው፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሡ በጣም ተደስቶ ልጁ የባህሩን ንጉስ ይዞ እንዲያመጣው ነገረው፡፡ ልዑሉም ደግና ደፋር ስለነበረ የአባቱን ትዕዛዝ በማክበር ሁለት ረዳቶችን ይዞ የባህሩን ንጉስ ሊይዝ ሄደ፡፡ የባህሩንም ንጉስ ፍለጋ ጀምረው ከብዙ በጣም አድካሚና አሰልቺ ትግል በኋላ የባህሩን ንጉስ መያዝ ቻሉ፡፡ የባህሩም ንጉስ በወርቅ የተሸፈነ ነበር፡፡
የባህሩም ንጉስ ልዑሉን “አባትህ እይታውን ያጣው በተፈጥሮ ስለሆነ እኔ ልረዳው አልችልም፡፡ የባህር ንጉስም ስለሆንኩ ልትገድለኝ አይገባም፡፡” አለው፡፡
ልዑሉም ሊለቀው ወሰነ፡፡
በዚህ ጊዜ የባህሩ ንጉስ ልዑሉን “ህይወቴን ስላተረፍክልኝ በማንኛውም ጊዜ እርዳታዬን ስትፈልግ ወደ ባህሩ ዳርቻ መጥተህ ብትጠራኝ መጥቼ እረዳሃለሁ፡፡” አለው፡፡
ልዑሉም ወደ አባቱ ተመልሶ የባህሩን ንጉስ መያዝ እንዳልቻለ ነገረው፡፡ ነገር ግን ወታደሮቹ ልዑሉ የባህሩን ንጉስ ይዞት እንደነበርና ከዚያም እንደለቀቀው ለንጉሱ በሚስጥር ነገሩት፡፡
ንጉሱም በጣም ተበሳጭቶ “ከአሁን በኋላ እሱ ልጄ አይደለም፡፡ ውሰዱና ግደሉት፡፡” ብሎ አዘዘ፡፡
ወታደሮቹም ወደሚገደልበት ቦታ ወሰዱት፡፡
ነገር ግን ግድያውን ከመፈፀማቸው በፊት “አንተ ጥሩ ሰውና ደግ በመሆንህ አንገድልህም፡፡ እንልቀቅህና ከአገር ጥፋ፡፡ እኛ ለአባትህ እንደገደልንህ እንነግረዋለን፡፡” አሉት፡፡
እናም ልዑሉ ጉዞውን ጀመረ፡፡ በመንገዱም ላይ አዳኞቹ አንዲትን ሚዳቋ ሲያሳድዱ አየ፡፡ ሚዳቆዋም ወደ ልዑሉ መጥታ ከአዳኞቹ እንዲያድናት ተማፀነችው፡፡ ልዑሉም የሚዳቆዋን ቀንድ በመያዝ አዳኞቹ እስኪመጡ ጠበቃቸው፡፡
አጠገቡም ሲደርሱ “ይህቺ ሚዳቋ የእኔ ናት፡፡ የእናንተ በዚያ በኩል ሄዳለች፡፡” አላቸው፡፡
አዳኞቹም አምነውት ወደጠቆማቸው ቦታ አመሩ፡፡ ሚዳቆዋም ውለታዋን እንደምትከፍል ቃል ገብታ ሄደች፡፡
ልዑሉም መንገዱን ቀጠለ፡፡ በመንገዱ ላይ ህፃናት አንድ መሬት ውስጥ የሚኖር ትንሽ እንስሳ (አይጥ) ሊገድሉ ሲሉ ደረሰ፡፡ ልጆቹም ዓይጡን እያሳደዱት ሳለ ልዑሉ ጋቢውን አውልቆ ዓይጡ ላይ በመወርወር ከጥቃት ከለለው፡፡
ልጆቹም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ “ልጆች አዳምጡኝ፣ አይጡ መሬት ውስጥ ገብቷል፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ልጆቹ ተመልሰው ሲሄዱ አይጡ ከጋቢው ስር ወጥቶ አንድ ቀን ውለታውን እንደሚከፍል ቃል ገብቶ ሄደ፡፡
ከዚያም ልዑሉ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከረጅም ጉዞ በኋላ ከወርቅ የተሰራ ቤት አጠገብ ደረሰ፡፡ ወደ በሩም ጠጋ ብሎ ዘበኛውን የማን ቤት እንደሆነ ጠየቀው፡፡
ዘበኛውም “በጣም አደገኛ የሆነች ሴት ቤት ነው፡፡” ብሎ ብዙ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ካሳየው በኋላ “ሴትየዋ ድብብቆሽ መጫወት ትወዳለች፡፡ እነዚህ የምታያቸው ሰዎች የሞቱት ከእርሷ ጋር ለመጫወት በመስማማታቸው ነው፡፡ ተደብቀው ስታገኛቸው ትገድላቸዋለች፡፡ ስለዚህ አንተም አርፈህ ብትሄድ ይሻልሀል፡፡” አለው፡፡
ልዑሉ ግን ከአደገኛዋ ሴትዮ ጋር ድብብቆሽ መጫወት እንደሚፈልግ ተናግሮ ወደ ቤቱ ውስጥ ገባ፡፡
ሴትየዋም “ሶስት ወይም አራት ቀናትን እሰጥህና ትደበቃለህ፡፡ ከዚያም ካገኘሁህ እገድልሃለሁ፡፡ ካላገኘሁህ ግን ቤቱ ያንተ ይሆንና ታገባኛለህ፡፡” አለችው፡፡
ልዑሉም በዚህ ተስማምቶ ጨዋታውን ከመጀመሩ በፊት ግን ወደ ባህሩ ሄዶ የባህሩን ንጉስ ከጠራው በኋላ “ከዚህች ሴት እንድትደብቀኝ እፈልጋለሁ፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ የባህሩ ንጉስ ልዑሉን ውጦ ደበቀው፡፡
ጨዋታውም ተጀመረ፡፡ ሴትየዋም ዓለምን ሁሉ የሚያሳያትን መሣሪያ አንስታ ትፈልገው ጀመር፡፡ ነገር ግን አላገኘችውም፡፡ በመጨረሻ ግን ከአሣ ነባሪው ሆድ ውስጥ አየችው፡፡
እናም የጨዋታው ቀን ሲያልቅ ልዑሉ ከአሣ ነባሪው ሆድ ውስጥ ወጥቶ ወደ ሴትየዋ ሄደ፡፡
እሷም “ላገኝህ በጣም ሞከርኩ፡፡ በመጨረሻ ግን የአሣ ነባሪው ሆድ ውስጥ አየሁህ፡፡” አለችው፡፡
ልዑሉም ልትገድለው እንደሆነ በማሰብ በጣም ደነገጠ፡፡ ነገር ግን ሴትየዋ ሌላ እድል እንደምትሰጠው ነገረችው፡፡
በዚህ ጊዜ ልዑሉ ወደ ሚዳቆዋ ሄዶ ከሴትየዋ እንድትደብቀው ለመናት፡፡ ሚዳቆዋም በጣም ሩቅ ወደሆነ ቦታ ወስዳው ከአንድ ትልቅ ዋሻ ውስጥ ደበቀችው፡፡ ሴትየዋም መሣሪያዋን በመጠቀም እንደገና ከብዙ ፍለጋ በኋላ ከአንድ ትልቅ ተራራ ስር አየችው፡፡ የጨዋታው ቀን ባለቀም ጊዜ ልዑሉ ወደ እርሷ ዘንድ ሲሄድ ከብዙ ልፋት በኋላ ከአንድ ተራራ ስር እንዳየችው ነገረችው፡፡ ልዑሉ አሁንም የምትገድለው መስሎት ደነገጠ፡፡ ነገር ግን ሴትየዋ አሁንም አንድ የመጨረሻ እድል እንደምትሰጠው ነገረችው፡፡
በዚህ ጊዜ ከመሬት ውስጥ ወደምትኖረው አይጥ ዘንድ ሄዶ “ከዚህች ሴት እንድትደብቂኝ እፈልጋለሁ፡፡” አላት፡፡
አይጧም ከመሬት ስር ወስዳው ከብዙ ጉዞ በኋላ ከጂኒዎች ዙፋን ስር ደበቀችው፡፡
ሴትየዋም በመሳሪያዋ ብትፈልግ፣ ብትፈልግ አሁን ልታገኘው አልቻለችም፡፡
የጨዋታው ቀን ባለፈ ጊዜ ልዑሉ ከመሬት ውስጥ ወጥቶ ወደ ሴትየዋ ሄደ፡፡
ሴትየዋም “ሁሉም ቦታ ፈለኩህ፤ ነገር ግን ላገኝህ አልቻልኩም፡፡” አለችው፡፡
ስለዚህ ልዑሉ ቤቷን ወስዶ ካገባት በኋላ በደስታ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|