ፃዲቁ ሰው
በአብዱልራህማን አብዱላሂ የተተረከ
በድሮ ጊዜ ራሱን ሙሉ ለሙሉ ለአምላክ ቃል ያስገዛ ፃዲቅ ሰው ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ብቻውን ፀሎት ለማድረስ ፈልጎ ፀጥ ወዳለ ቦታ እየሄደ ሳለ አንድ የመስኖ እርሻ ቦታ ሲደርስ መንደሪን ውሃው ላይ ሲንሳፈፍ አየ፡፡ መንደሪኑንም አንስቶ በላውና ለፀሎት መዘጋጀት ጀመረ፡፡
በዚህ ጊዜ መንፈስ ተገለጠለትና “ለአምላክ የተገዛሁ ነኝ እያልክ ለምንድነው የሌላ ሰው ፍሬ አንስተህ የበላኸው?” አለው፡፡
ወዲያውኑ ቅዱሱ ሰው በድርጊቱ ተፀፅቶ ወደ እርሻው በመመለስ የመንደሪን እርሻ አጠገብ ደረሰ፡፡
ወደ እርሻው ባለቤትም ሄዶ “ከዛፍ ላይ የወደቀ አንድ የመንደሪን ፍሬ ውሃው አምጥቶት ስላየሁ በልቸዋለሁና ይቅር በለኝ፡፡” አለው፡፡
የእርሻው ባለቤት ግን ይቅር አልልህም ስላለው ቅዱሱ ሰው በጣም አዘነ፡፡ የእርሻውም ባለቤት “ይቅርታ እንዳደርግልህ ከፈለክ የምጠይቅህን ነገር ማድረግ አለብህ፡፡” አለው፡፡
ፃዲቁም ሰው ተስማማ፡፡
ገበሬውም “አይንና እግሮች የሌሏትን ልጄን ካላገባህ ይቅር አልልህም፡፡” አለው፡፡
ፃዲቁም “ችግር የለም፣ ይቅር ካልከኝ አገባታለሁ፡፡” አለው፡፡
ከዚያም ወደ እርሻው ባለቤት ቤት ሄደው ፃዲቁ ሰው ልጅቷ የት እንዳለች ጠየቀው፡፡
ባለቤቱም “ልጄን ከማየትህ በፊት ስለጋብቻው ዝርዝር ሁኔታ እንነጋገር፡፡” አለው፡፡
ፃዲቁም ሰው የተባለውን ሁሉ አደረገ፡፡
ልጅቷም ከተደበቀችበት ቦታ ስትወጣ ሁለት ዓይኖችና ሁለት እግሮች ያሏት ከመሆኗም በላይ በጣም ቆንጆ ነበረች፡፡
ፃዲቁም ሰው የእርሻውን ባለቤት “ዓይኖችና እግሮች የሏትም ብለኸኝ አልነበረም እንዴ?” ሲለው፡፡ እሱም “ልልህ የፈለኩት ልጄ ክፉ ነገር አድርጋ የማታውቅና በባህሪዋም የተሳሳተ መንገድ ያልያዘች መሆኗን ልነግርህ ፈልጌ ነው፡፡” አለው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|