አጣቢዋ ሴት ወይም የሌላ የሚፈልግ የራሱን ያጣል
በዘይነባ አቢበከር ደረሞ የተተረከ
ከብዙ ዘመናት በፊት ኑሮዋን ልብስ በማጠብ ላይ የመሰረተች አንዲት አዛውንት ሴት ነበረች፡፡ ሴትየዋም አንድ ወጣት ልጅ ረዳት ነበራት፡፡ ወደ ወንዝ አብረው በመሄድ ሙሉ ቀን ልብስ ሲያጥቡ ውለው ያገኙትን ገንዘብ ለምግባቸው ካዋሉት በኋላ ቀሪውን አዛውንቷ ሴት ታስቀምጣለች፡፡ አዛውንቷ ሴት ገንዘቡን ማስቀመጥ ስትፈልግ ወጣቱን ልጅ “ወደ ሽንት ቤት ልሄድ ነው፡፡” ትለዋለች፡፡
ሰዋራ ቦታም ስትደርስ ገንዘቡን እዚያ ትደብቀዋለች፡፡ ልጁ ግን ሴትየዋ ወደ ሽንት ቤት ለምን ሁልጊዜ ተደብቃ መሄድ እንደምትፈልግ ስላልገባው አንድ ቀን ታዲያ “ምን እየሰራች እንደሆነ ማየት አለብኝ፡፡” ብሎ በማሰብ ተደብቆ ተከትሏት ሄደ፡፡
ከዚያም ሴትየዋ ገንዘቧን በድብቅ ቦታ እንደምታስቀምጥ አይቶ ገንዘቡን ወሰደው፡፡
በሚቀጥለው ቀን አዛውንቷ ሴት ተጨማሪ ገንዘብ ለማስቀመጥ ወደ ቦታው ስትሄድ ገንዘቡን አጣችው፡፡ ገንዘቧንም የምታስመልስበትን ዘዴ በመፈለግ ልብሶች እያጠበች ሳለ እንዲህ ብላ ዘፈነች፤
“ለማሰብ ቅድሚያ የሚሰጥ
በመጨረሻ ተጨማሪ ያገኛል፡፡”
በዚህ ጊዜ ልጁ ዘፈኗ ስለገባው “ገንዘቡን ልመልስና ተጨማሪ ገንዘብ ስታስቀምጥ በኋላ ሁሉንም ወስደዋለሁ፡፡” ብሎ አሰበ፡፡ ገንዘቡንም መለሰ፡፡ አዛውንቷም ሴት ገንዘቧን መልሳ አገኘችው፡፡ ከዚያም ወደ ወንዙ ሄዳ ልብስ እያጠበች “የሌሎችን ንብረት የሚፈልግ የራሱን ያጣል፡፡” እያለች መዝፈን ጀመረች፡፡
በዚህ ጊዜ ልጁ እንደተበለጠ ስለገባው ያለምንም ገንዘብ ባዶ እጁን ቀረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|