ብልኋ ሴት
በአብዱልራህማን አብዱላሂ የተተረከ
ከረጅም ጊዜ በፊት ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስትየው ቤተሰቡን ለመደገፍ ውጪ እየሄደች ስትሰራ ባልየው ግን በቤት ውስጥ ያለምንም ስራ ተቀምጦ ይውል ነበር፡፡ በመጨረሻም ሚስትየው በባሏ ስራ ፈትነት ትሰላች ጀመር፡፡
እንዲህም አለችው “ዝም ብለህ ቤት ውስጥ ከምትቀመጥ ለምን ከተማ ውስጥ ከብለል፣ ከብለል አትልም፡፡”
ባልየውም ሚስቱ የእውነት ተንከባለል ያለችው መስሎት ወደ ከተማ ሄዶ ሙሉ ቀን ሲንከባለል ውሎና በጣም ቆሽሾ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
ሚስቱም ባየችው ጊዜ በጣም ተገርማ “ተንከባለል ያልኩህ እኮ እንድትንከባለል ማለቴ ሳይሆን ዞር ዞር ብለህ ተመለስ ለማለት ፈልጌ ነበር፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም “ሙሉ ቀን ቤት ውስጥ ብትውል ይሻላል፡፡ ከቤት የትም አትሂድ፡፡” አለችው፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በጣም ስለሰለቻት ወደ መስጊድ ሄዶ ከደጃፉ ላይ መፅሃፍ ይዞ እንዲቀመጥ አዘዘችው፡፡ ከዚያም ባልየው ወደ መስጊድ ደጃፍ በመሄድ ሙሉ ቀን እዚያው ያሳልፍ ጀመር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ከብቶች የጠፉባቸው ሁለት ሰዎች በመስጊዱ ደጃፍ ሲያልፉ መፅሐፍ ይዞ የተቀመጠውን ሰው አይተው ትንቢት ተናጋሪ መሰላቸው፡፡
ከዚያም ወደ ሰውየው ጠጋ ብለው “ላሞቻችን ወዴት እንደሄዱ ከነገርከን ብዙ ገንዘብ እንሰጥሃለን፡፡” አሉት፡፡
ባልየው ማንበብም ሆነ መፃፍ አይችልም ነበር፡፡ ነገር ግን የሚያነብ መስሎ መፅሀፉን መግለፅ ጀመረ፡፡
ከዚያም “ትኩስ ቅቤ መዋጥ አለባችሁ፡፡” አላቸው፡፡
ከሁለቱ ሰዎች አንዱ “ላሞቻችንን እንደታገኝልን እንጂ ቅቤ ልንበላ አልመጣንም፡፡” አለው፡፡
ሁለተኛው ሰው ግን “እስኪ እንሞክር፡፡” ብሎ ቅቤ ገዝቶ ዋጠ፡፡ ወዲያው ሆዱን ስላመመው ሰዋራ ስፍራ ፈልጎ ለመፀዳዳት ሄደ፡፡ ሰዋራ ስፍራም ለመፈለግ በሄደ ጊዜ ከአንድ የፈራረሰ ቤት ውስጥ ላሞቹን አገኛቸው፡፡ በዚህም በጣም ተደስተው ለባልየው ብዙ ገንዘብ ከፈሉት፡፡
ባልየውም ወደቤት ሄዶ ገንዘቡን ለሚስቱ አሳያት፡፡
እሷም “ይህን ገንዘብ ከየት ነው ያመጣኸው?” ብላ ጠየቀችው፡፡
እሱም ታሪኩን በሙሉ ነገራት፡፡
አንድ ቀን ታዲያ የንጉሱ ካዝና ከቤተ መንግስት ተሰረቀ፡፡ ንጉሱም አገልጋዮቹን በሙሉ ሰብስቦ ካዝናውን ፈልገው እንዲያመጡለት አዘዛቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ላሞች ጠፍተውባቸው በባልየው እርዳታ ያገኙዋቸው ሁለት ሰዎች ወደ ንጉሱ ሄደው “እኛ ሌቦቹ ካዝናውን ወዴት እንደወሰዱት የሚነግርህ ትንቢት ተናጋሪ እናውቃለን፡፡” ብለው ሰውየውን ለንጉሱ አመላከቱት፡፡
ባልየውም ይህንን በሰማ ጊዜ ከሚስቱ ጋር ተመካከረ፡፡
ሚስትየውም “ወደ ንጉሱ ሄደህ ‘እስከ ነገ ጊዜ ስጠኝና ነገ ጠዋት ካዝናህን አገኝልሃለሁ፡፡’ በለው፡፡ እስከ ጠዋት ካዝናውን ካላገኘነው ተያይዘን እንጠፋለን፡፡” አለችው፡፡
እናም ባልየው ወደ ንጉሱ ሄዶ “ይህ ስራ ትንሽ ከበድ ስለሚል እስከ ነገ ጠዋት ጊዜ ስጠኝ፡፡” አለው፡፡
ሆኖም ካዝናውንም ሆነ ሌቦቹን ማግኘት አልቻሉም፡፡
ሌቦቹ ግን ደጃፉ ላይ ያሉትን ጠባቂዎች ማለፍ ስላልቻሉ ከቤተ መንግስቱ ውስጥ ተደብቀው ነበር፡፡ ሚስትየው ለመጥፋት እቃቸውን ማዘጋጀት ጀመረች፡፡ በዚህ ጊዜ ባልየው ካዝናውን የማግኘቱ ሥራ እንደተሰጠው ሌቦቹ ስለሰሙ እንደምንም ብለው ከቤተመንግስቱ ግቢ ውስጥ ወጥተው ካዝናዎቹን እዚያው ግቢው ውስጥ ትተው ወደ ሰውየው ቤት አመሩ፡፡ ሰውየውንም አግኝተው ካዝናዎቹ እዚያው ቤተ መንግስቱ ግቢ ውስጥ እንዳሉ ከነገሩት በኋላ ለህይወታቸው ንጉሱን እንዲማፀንላቸው ለመኑት፡፡
እናም ሰውየው ወደ ንጉሱ ሄዶ “ከብዙ አድካሚ ፍለጋ በኋላ ሌቦቹን አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን እንደማይነኩ ቃል ገብቼላቸዋለሁ፡፡” በማለት ንጉሱ እንዳይነካቸው ተማፀነው፡፡ ከዚያም ካዝናዎቹ የት እንዳሉ ለንጉሱ ነገረው፡፡
በዚህም ንጉሱ በጣም ስለተደሰተና በስራውም ስለረካ በየሳምንቱ ብዙ ገንዘብ ይልክለት ጀመር፡፡
ነገር ግን በከተማው ውስጥ ያሉት ሌሎች ትንቢት ተናጋሪዎች በማመፅ “ይህ ሰው ካለምንም እውቀት ከእኛ በላይ እየተከፈለው ነው፡፡” በማለት ተቃውሟቸውን አሰሙ፡፡
በዚህን ጊዜ ንጉሱ የተሻለውን ትንቢት ተናጋሪ ለመምረጥ በማሰብ ሁሉም ትንቢት ተናጋሪዎች የተሳተፉበት የክርክር መድረክ አዘጋጀ፡፡
ከዚያም ባልየው ለሚስቱ “እኔ ማንበብና መፃፍ እንኳን አልችልም፡፡ እንዴት ነው ከእነዚህ ትንቢት ተናጋሪዎች ጋር የምከራከረው?” አላት፡፡
ሚስቱም “አትጨነቅ፡፡ ዝም ብለህ ብቻ ሂድ፡፡” አለችው፡፡
ወደ ቤተመንግስቱም በሄደ ጊዜ የከተማው ህዝብ በሙሉ እዚያ ተሰብስቦ ስላየ በጣም ፈርቶ አዳራሹ መግቢያ ላይ ቆሞ ንጉሱ ወደ እርሱ እንዲመጣ ጠራው፡፡ ይህ አንድ ምስኪን ሰው ንጉሱን ወደ እርሱ ሲጠራው ባዩ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ ተገረሙ፡፡
ንጉሱም ከመቀመጫው ተነስቶ ከአዳራሹ መግቢያ ላይ ወደጠራው ሰው ሲሄድ ወዲያውኑ አዳራሹ ፈረሰ፡፡ ንጉሱና ሰውየው ከጉዳት ሲያመልጡ ሌሎቹ ትንቢት ተናጋሪዎች ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ንጉሱ በባልየው ስለተደነቀ “የዚህን ሰው ቃል ማንም ሰው ሊጠራጠር አይችልም፡፡” ብሎ አወጀ፡፡ ማንም ሰው ከእርሱ ጋር እንዳይወዳደርም ከለከለ፡፡
ከዚያች ቀን ጀምሮ ይህ ሰው ያለምንም ችግር በመኖር የተከበረና በጣም ትልቅ ወርሃዊ ደሞዝ ያለው ሰው ሆነ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|