ዓይን ያየውን ገንዘብ ይገዛዋል ወይም ሃብታሙ ነጋዴ
በአብዱል ራህማን አብዱላሂ የተተረከ
ከብዙ አመታት በፊት አንድ ሃብታም ነጋዴ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሱቁ በር ላይ “አይኖቼ የሚያዩትን ማንኛውም ነገር መግዛት እችላለሁ፡፡” የሚል ማስታወቂያ ለጠፈ፡፡ ንጉሱም በከተማዋ ውስጥ እየተዘዋወረ ሳለ የነጋዴውን ሱቅ ሲጎበኝ ማስታወቂያውን አየ፡፡
ከንጉሱ አማካሪዎች አንዱ ንጉሱን “ይህ ነጋዴ በጣም ባለጌ ነው፡፡ ይህንን ማስታወቂያ የለጠፈው የእርሶን ልጅም ቢሆን ወደ ቤቱ እንደሚያስመጣት ለማሳየት ስለሆነ እርስዎንም እየተሳደበ ነው፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ወደ ነጋዴው ሱቅ ጎራ ብሎ ነጋዴውን “የእኔን ልጅ ጨምሮ ሌላ የፈለከውንም ነገር እዚህ ማምጣት እችላለሁ ማለትህ ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ነጋዴውም “አዎ፣ እችላለሁ፡፡ አንድ ቀን ቁረጥና በዚያን ዕለት ልጅህን ወደዚህ ሱቅ ካላመጣኋት በስቅላት ልቀጣ፡፡” አለ፡፡
ንጉሡም በዚህ ተስማማ
ነጋዴውም ወደ አንድ የወርቅ አንጥረኛ በመሄድ “እኔ በጣም ሃብታም ነኝ፡፡ የቻልኩትን ያህል ወርቅ ልገዛ መጥቻለሁና አንዲት ከወርቅ የተሰራችና ሰው ሊያስቀምጥ የሚችል ትልቅ ሆድ ያላት ግዙፍ ላም አዘጋጅልኝ፡፡” አለው፡፡
ከዚያም የወርቋን ላም ለሰዎች እያስከፈለ ያሳይ ጀመር፡፡ ይህ ጉዳይ በጣም እየታወቀ ስለሄደ ዜናው በከተማው ውስጥ በሙሉ ተናኘ፡፡ ሰዎች ከሁሉም ቦታዎች መጉረፍ ጀመሩ፡፡
ልዕልቷም ስለዚህ ጉዳይ በሰማች ጊዜ ላሟን ማየት ትችል ዘንድ አባቷ ላሟን ወደ ቤተ መንግስት እንዲያስመጣላት ጠየቀችው፡፡ ንጉሱም ወታደሮቹ ላሟን ሄደው እንዲያመጧት አዘዛቸው፡፡
ነጋዴውም በላሟ ሆድ ውስጥ ተደብቆ ሳለ ላሟ ተወስዳ ልዕልቷ መኝታ ቤት ውስጥ ተቀመጠች፡፡ ልዕልቷም ወርቃማዋን ላም ባየች ጊዜ ሰዎቹን የትም እንዳይወስዷት አዛቸው ተኛች፡፡
በዚህ ጊዜ ነጋዴው ከላሟ ሆድ ውስጥ ወጥቶ ቀለበቱን ከልዕልቷ ቀለበት ጋር አቀያይሮ ወደ ላሚቷ ሆድ እቃ ተመለሰ፡፡ ልዕልቷም ከእንቅልፏ ስትነቃ ቀለበቷ ተቀይሮ ስላየች እንደገና የተኛች በመምሰል የሚሆነውን ነገር ለማየት አንቀላፋች፡፡ ከዚያም ነጋዴው ልዕልቷ እንደገና የተኛች መስሎት ከላሚቷ ውስጥ ተንፏቆ ሲወጣ ልዕልቷ ያዘችው፡፡ ከዚያም እንዳትከዳው ለመናት፡፡ እሷም እሺ ብላ ደንገጡሮቿ ብዙ ምግብ እንዲያመጡላት አዘዘቻቸው፡፡ ንጉሱም ልጁ ጥሩ የምግብ ፍላጎት እንዳላት ሲሰማ ደስ አለው፡፡
ከዚያም ነጋዴውና ልዕልቷ በጣም እየተቀራረቡ ሄደው ብዙ ነገር ከተጨዋወቱ በኋላ ልዕልቲቱ በፍቅሩ ወደቀች፡፡ ነጋዴው ግን ወርቃማዋ ላም ወደሱቁ እንድትመለስለት ቢፈልግም ልዕልቲቱ አሻፈረኝ አለች፡፡ በዚህ ዓይነት ለአንድ ወር በልዕልቷ መኝታ ቤት ከቆዩ በኋላ ላሚቷን ለመልቀቅ ተስማማች፡፡ በዚህን ጊዜ የነጋዴው የሞት ቀጠሮ ሁለት ቀናት ብቻ ቀርተውት ነበር፡፡ ንጉሱም ነጋዴውን ወደ ቤተ መንግስቱ አስጠርቶ ትሰቀላለህ አለው፡፡
ነጋዴውም “ከተሰቀልኩ መሰቀል የምፈልገው እያንዳንዱ የከተማው ዜጋ ባለበት ነው፡፡” አለ፡፡
በመሰቀያውም ቀን ሁሉም የከተማው ዜጎች በተሰበሰቡበት ነጋዴው የንግስቲቱን ቀለበት ከኪሱ አውጥቶ ለንጉሱ አሳየው፡፡
“ይህ ቀለበት የማን ነው?” በማለት ነጋዴው ጠየቀ፡፡
ንጉሱም ቀለበቱን በተመለከተ ጊዜ የልጁ ቀለበት እንደሆነ አወቀ፡፡ ነጋዴውም “ልጅህ የማንን ልጅ በሆዷ እንደተሸከመች እንድትጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡” አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ልዕልቷ ወደ ነጋዴው መሰቀያ ቦታ ተጠርታ ያረገዘችው የማንን ልጅ እንደሆነ ስትጠየቅ የነጋዴውን ልጅ እንዳረገዘች በከተማዋ ዜጎች ሁሉ ፊት አመነች፡፡
ንጉሱም በሁኔታው አፍሮ “ቀድሞውኑ ልጄን በሚስትነት ልሰጥህ ይገባ ነበር፡፡” አለው፡፡
በዚህ ሁኔታ ልዕልቲቱን ለነጋዴው ከዳራት በኋላ ከጥቂት ቆይታ በኋላም ንጉሱ ሲሞት ነጋዴው ከተማዋን ለብዙ፣ ብዙ ዘመናት ገዛ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|