አህያና ጅብ
በአብዱል ራህማን አብዱላሂ የተተረከ
ከብዙ ዘመን በፊት ጅብ በሰማይ ላይ ነበር የሚኖረው፡፡ እዚያም ሆኖ ይጮህ ነበር፡፡ አህዮቹም የጅቡን ድምፅ ከሰማይ ላይ በሰሙ ጊዜ የዚህን የቆንጆ ድምፅ ባለቤት የሆነውን ጅብ ወደ መሬት እንዲያወርድላቸው አምላካቸውን በፀሎት ይለምኑ ነበር፡፡
ነገር ግን አምላክ “እርሱን ወደመሬት ካወረድኩት ይበላችኋል፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱ ግን “አይበላንም ይህንን እንስሳ እባክህ ላክልን፡፡” አሉት፡፡ በዚህ አይነት አያ ጅቦ ወደምድር ሲመጣ አህዮቹ ሳር ይበላ ዘንድ ጋበዙት፡፡ ጅቡም እምቢ ባለ ጊዜ ሌላ ምን መብላት እንደሚፈልግ ጠየቁት፡፡
እሱም “ከስጋ በስተቀር ሌላ ነገር በፍፁም አልበላም፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ አህዮች ተሰባስበው ስለችግሩ በመወያየት አንድ ያረጀ አህያ ሊሰጡት ወሰኑ፡፡
ከትንሽ ቆይታ በኋላ ጅቡ አሁንም ራበኝ ሲላቸው ጆሮዎቻቸውን በሙሉ ቆርጠው ሰጡት፡፡
አንድ ቀን ታዲያ በዚህ አይነት እየኖሩ ሳለ ጅቡ ዘመድ ስለሞተበት አህዮቹ መጥተው እንዲያስተዛዝኑት ጠየቃቸው፡፡ ሁሉም አህዮች ወደ ጅቡ ቤት ሄዱ፡፡
ነገር ግን አህዮቹ ለጅቡ የሚሰጡት ምንም ነገር ስላልነበራቸው ምን ሊያደርጉለት እንደሚፈልግ ጠየቁት፡፡ ከንፈሮቻቸውን ቆርጠው አብስሎ እንዲበላ ሰጡት፡፡
ጅቡም ጥርሶቻቸውን ባየ ጊዜ በመናደድ “እኔ እያዘንኩ እናንተ እንዴት ትስቃላችሁ?” ሲላቸው አህዮቹ ፈርተው መሮጥ ጀመሩ፡፡ እሱም እያሳደደ ግማሾቹን ይዞ በላቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ አህያና ጅብ ጠላቶች ሆኑ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|