ወንድምና እህት
በአይ ኑሪያ ዩሱፍ አብደላ የተተረከ
በዚህ ታሪክ የመጨረሻ ክፍል ውስጥ የአይ ኑሪያ ዩሱፍ አብደላና የናጃሃ አብዱል ከሪም ቤተሰብ ሁለት ትረካዎች ተካተዋል፡፡
ሁለት እህታማቾች ነበሩ፡፡ አንደኛዋ እህት ናዲራ ስትባል ሁለቱም ከእናትና አባታቸው ጋር ይኖሩ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወላጆቻቸው ወንድማቸውን ጠርተው ለራሱ ሚስት እንዲፈልግ ነገሩት፡፡ እሱም ሚስት ፍለጋ ቢወጣም በልቡ ውስጥ ግን እህቱን ማግባት ነው የፈለገው፡፡
ስለዚህ ወደቤት ተመልሶ ለወላጆቹ “ከእህቴ ከናዲራ የምትሰተካከል ሚስት ማግኘት አልቻልኩም፡፡” ብሎ ዋሻቸው፡፡
አሁንም ደግመው እንዲፈልግ ላኩት፡፡
እርሱም ተመልሶ መጥቶ “እህቴን የምትስተካከል ልጃገረድ አላገኘሁም፡፡” ብሎ ነገራቸው፡፡
ከዚያም እናትየው ባሏን “ልጃችን የምትሆነውን ሴት በከተማው ሙሉ ቢፈልግም እህቱን የምትሰተካከል ልጃገረድ አላገኘም፡፡” አለችው፡፡
አባትየውም በጣም ተበሣጭቶ “አብደሻል እንዴ? ታዲያ እህቱን እንዲያገባ ነው የምትፈልጊው? እንደዚህ አይነቱን መዘበራረቅ ከእንግዲህ መስማት አልፈልግምና ብታርፊ ይሻልሻል፡፡” ብሎ አስጠነቀቃት፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ልጁ ከጓደኞቹ ጋር እንጨት ለመቁረጥ ወደ ጫካ ሄዶ ናዲራን እንዴት ጠልፎ ወስዶ ሊያገባት እንደሚችል መወያየት ጀመሩ፡፡
ነገር ግን የናዲራ ታናሽ ወንድም ይህንን ሴራቸውን ስለሰማ ወደ ቤት ሮጦ በመሄድ ለናዲራ ይነግራታል፡፡ ሴራውን ያቀነባበረችው ግን እናትየው ስትሆን እቅዱ ናዲራን ለወንድሟና ለጓደኞቿ ምሳ እንድታደርስላቸው መላክ ነበር፡፡
እናም ትንሹ ወንድሟ “አዳምጭኝ፣ ምሳቸውን የሚበሉበት ቦታ ስትደርሺ ዛፍ ስር ተቀምጠው ታገኛቸዋለሽ፡፡ ምሳቸውን ከማድርስሽ በፊት ሳያዩሽ ቀስ ብለሽ ደርሰሽ አይናቸው ውስጥ በርበሬ በመጨመር ሮጠሽ ተመለሺ፡፡” ብሎ ነገራት፡፡
ከዚያም እናትየው ጠርታት ለወንድሟና ለጓደኞቹ ምሳ እንድታደርስላቸው ስትነግራት ናዲራም ትዕዛዙን ተቀብላ ወደ እነርሱ ሄደች፡፡
እርሷም ወደ እነርሱ መምጣቷን ባዩ ጊዜ ተደስተው “ናዲራ እየመጣች ነው፤ ናዲራ መጣሽ! መጣሽ!” አሏት፡፡
በዚህን ጊዜ በርበሬውን አይናቸው ውስጥ ጨመረችባቸው፡፡ እነርሱም መጮህና መንጫጫት ሲጀምሩና አይናቸው በታወረ ጊዜ እሷ ሮጣ አመለጠች፡፡ አንድ በጣም ትልቅ ዛፍ በማዶ በኩል ያለው ጠንካራና ፈጣን ወንዝ ድረስ እስክትደርስም ሩጫዋን አላቆመችም፡፡
ለአምላክም እንዲህ እያለች መፀለይ ጀመረች፤
“እባክህ አንተ ውሃ ቁምልኝ
እባክህ አንተ ውሃ ቁምልኝ
አላህ በፈጠረው ምድር ላይ፡፡” አለች፡፡
በዚህ ጊዜ ውሃው ጠፋ፡፡ ደግሞም እንዲህ እያለች ፀለየች፤
“አንተ ዛፍ ሆይ፣ እባክህ አጎንብስ
አንተ ዛፍ ሆይ፣ እባክህ አጎንብስ
አላህ ወደፈጠረው ምድር፡፡” አለች
በዚህም ጊዜ ዛፉ ወዲያው ስላጎነበሰ ዛፉ ላይ ወጣች፡፡
ከዚያም “አንተ ዛፍ ሆይ፣ ቀጥ በል
አንተ ዛፍ ሆይ፣ ቀጥ በል
አላህ በፈጠረው ምድር ላይ፡፡” አለች፡፡
ዛፉም ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡ ከዚያም እንዲህ አለች፤
“አንተ ውሃ ሆይ፣ እንደገና ፍሰስ
አንተ ውሃ ሆይ፣ እንደገና ፍሰስ
አላህ በፈጠረው ምድር ላይ፡፡” አለች፡፡
በዚህ ጊዜ አንዲት ወፍ መጥታ ቅርጫት ለመስሪያ የሚሆን ትልቅ ወስፌና የተለያየ ቀለም ያላቸው ሳሮች ሰጠቻት፡፡ በዚህ ሁኔታ በጣም የሚያማምሩ የሃደሪ ቅርጫቶችን እየሰፋች እዚያው መኖር ጀመረች፡፡
ወንድሟና ወላጆቿ ሲፈልጓት ቆይተው ወንዙን ተሻግረው በደረሱ ጊዜ ዛፉ አናት ላይ ቁጭ ብላ ሲያዩዋት ከእንስሳት በስተቀር እዚያ ጫፍ ላይ ማንም ሊኖር ስለማይችል አይናቸውን ማመን አቃታቸው፡፡
ስለዚህ ተጣርተው “እንደዚህ በጣም ረጅም ዛፍ ላይ የሰው ልጅ እንዴት ሊኖር ይችላል?” አሏት፡፡
እሷም “እንዴት ታላቅ ወንድም ባል ሊሆን ይችላል? እናም የራሴ አባት እንዴት አማቼ ሊሆን ይችላል? እንዴትስ እናቴ አማቴ ልትሆን ትችላለች? ይህ ታይቶም ተሰምቶም ያውቃል?” አለቻቸው፡፡
ከዚያም “ዛፉ ላይ እንዴት ልትወጪ ቻልሽ?” ብለው ጠየቋት
የናጃሃ ቤተሰብ የትረካው አጨራረስ
ልጅቷ በቤተሰቧ ከታናሽ ወንድሟ በቀር በጣም ስለተናደደች ወንዙ ውስጥ ገብተው በአዞ እንዲበሉ ስለፈለገች “ወንዙን በዋና አቋርጬ ነው ዛፉ ላይ የወጣሁት፡፡” አለቻቸው፡፡
በዚህን ጊዜ ሁሉም ወንዙ ውስጥ ገብተው ሊዋኙ ሲሞክሩ ስለሰመጡ አዞዎቹ በሏቸው፡፡ ታናሽ ወንድሟን ግን ዛፉን በተመለደው ግጥሟ ካስጎነበሰችለት በኋላ ከወንዙ ውስጥ አውጥታ አዳነችው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልዑል ወደ ወንዙ ሲመጣ ዛፉ ላይ ተቀምጠው አያቸው፡፡ በናዲራ ፍቅርም ስለተያዘ እንድታገባው ጠየቃት፡፡ እሷም “ምራቄ ከላይህ ላይ ካረፈ አገባሃለሁ፤ ካላረፈ ግን አላገባህም፡፡” ብላው እሱ ወዳለበት እቅጣጫ ስትተፋ ምራቋ ልዑሉ ላይ ስላረፈ ከዛፉ ወርዳ ልዑሉን በማግባት አብረው በደስታ መኖር ጀመሩ፡፡
የአይ ኑሪያ የትረካው አጨራረስ
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እረኛ ጥሩ ሣር ፍለጋ ወደ ወንዙ ሲመጣ ናዲራ የሃደሪን ቅርጫት ዛፍ ላይ ሆና ስትሰፋ አያት፡፡
እረኛው መናገርም ሆነ መስማት አይችልም ነበር፡፡ ወደ ጌታው ልዑልም ሮጦ “እምም ፣እምም፡፡” አለው፡፡ ልዑሉ ሊረዳው አልቻለም፡፡ እረኛው ግን ተመልሶ ወደ ወንዙ ሩጫውን ቀጠለ፡፡ ልዑሉም ተከትሎት ወንዙ ዳር በደረሱ ጊዜ እረኛው ወደ ናዲራ በመጠቆም ለልዑሉ አሣየው፡፡
ልዑሉም ወዲያው በፍቅሯ ወድቆ እንዲህ ሲል ጠየቃት “እዚህ ዛፍ ላይ እንዴት ልትወጪ ቻልሽ? እዚያ ላይ ሆነሽ ልደርስብሽ ስለማልችል ላገባሽ አልችልም፡፡ ምን ባደርግ ይሻለኛል?”
እሷም በግጥም እንዲህ አለችው፤
“የሰራሁትን ቅርጫት
በቅሎዋም አትችለው
ማንስ ይሸከምልኛል?” ካለች በኋላ “ይህንን ግጥም ድገመው” አለችው፡፡
እሱም ደገመው፡፡
ከዚያም “የምተፋብህ ምራቅ ወደ ወርቅነት ከተለወጠ አገባሃለሁ፡፡” ብላው ስትተፋበት ምራቋ ወደ ወርቅነት ተለወጠ፡፡
ከዚያም “ልጅቷ ቅርጫት ሰፍታለች፡፡
ማን ይሸከመዋል?” ካለች በኋላ “ይህንን ካልክ አገባሃለሁ፡፡” አለችው፡፡
እሱም ይህንን ግጥም አለ፡፡ እሷም ግጥሙን ለዛፉና ለውሃው ደገመችው፡፡ ከዚያም ከዛፉ ወርዳ በቤተመንግስት በትልቅ ድግስ ልዑሉን አገባችው፡፡
ታናሽ ወንድሟም አብሯት መጥቶ እዚያው መኖር ጀመረ፡፡
አንድ ቀን ከቤቱ አናት ላይ ሆና በመመልከቻ መሣሪያ (ቴሌስኮፕ) አርቃ ስትመለከት ሰዎች ወደ ቤቱ ሲመጡ አየች፡፡
ከዚያም “ይህ ወንድሜን ይመስላል፣ ይኸኛው ደግሞ አባቴን ይመስላል፣ ይህችኛዋም እናቴን ትመስላለች፡፡” አለች፡፡
ከልዑሉ ጋር እየኖረች ሳለ (እሷ እዚህ መኖሯን ሳያውቁ) ቤተሰቧ ከረጅም ፍለጋ በኋላ በጣም ስለደከማቸው ምግብ ሊለምኑ መጡ፡፡
የበሩ ጠባቂም “ምን ሆናችሁ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
“አንዲት ልጅ ጠፍታብን፡፡” ብለው መለሱ፡፡
ጠባቂውም “እንዴት ልትጠፋ ቻልች?” አላቸው፡፡
እነርሱም የሆነውን ሁሉ ነገሩት፡፡
እሱም “የልጃችሁ ስም ማን ነበር?” ብሎ ሲጠይቃቸው “ናዲራ” ብለው መለሱለት፡፡
“ከልጅቷ ጋር ያላችሁ ዝምድና ምንድነው?” ሲላቸው፤
“እኔ አባቷ ነኝ”
“እኔ እናቷ ነኝ”
“እኔ ደግሞ ወንድሟ ነኝ፡፡” እያሉ በየተራ መለሱ፡፡ ከዚያም ወደ ቤተመንግስቱ አስገብተው ምግብ፣ ውሀና ልብስ ከሰጧቸው በኋላ እየተዝናኑ ሳለ ናዲራ የእሷ ቤተሰብ መሆናቸውን እርግጠኛ ሳትሆን ብቅ አለች፡፡ ታዲያ እናቶች ልጆቻቸውን ስለማይሳሳቱ የእሷም እናት ወዲያው አወቀቻት፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|