ሼክ ናስረዲንና ስስታሙ ሰው
በሃጂ አብዱሰታር መሃመድ በሽር የተተረከ
በአንድ ወቅት በጣም ስስታም ነገር ግን በጣም ሃብታም የሆነ የናስረዲን ጎረቤት ነበር፡፡ ናስረዲን ግን በጣም ድሃ ነበር፡፡ ናስረዲንም አላህ 1000 ፓውንድ እንዲሰጠው ይፀልይ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ስስታሙ ሰው የናስረዲንን ፀሎት ሲሰማ የመስጊዱ ጣሪያ ላይ ወጥቶ 999 ፓውንድ ሊወረውርለት አሰበ፡፡ ወደ መስጊዱም በመሄድ ናስረዲን አምላኩ ገንዘብ እንዲሰጠው ሲፀልይ ስስታሙ ሰው ገንዘቡን ማዝነብ ጀመረ፡፡ ናስረዲንም በጣም ተደስቶ ገንዘቡን ከሰበሰበ በኋላ መቁጠር ጀመረ፡፡ በመጨረሻም 1 ፓውንድ መጉደሉን ሲያውቅ ወደ ሰማይ አንጋጦ “አምላክ ሆይ፣ 1 ፓውንድ አጉድለህብኛልና ዕዳ አለብህ፡፡” አለ፡፡
በሚቀጥለው ቀን ጎረቤቱ ወደ ናስረዲን ቤት ሄዶ “አዳምጥ፣ ፀሎትህን ሁሉ ሰምቻለሁ በፀሎትህም የለመንከውን ገንዘብ 1000 ፓውንድ ካነሰ አልቀበልም ማለትህን ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ግን 999 ፓውንድ ስሰጥህ ተቀብለሃል” አለው፡፡
ናስረዲንም “ስለምን እያወራህ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ውጣ ከቤቴ” አለው፡፡
ስስታሙም ሰው ወደ ዳኛ ወሰደው፡፡ መንገድ ከመጀመራቸው በፊት ግን ስስታሙ ሰው በቅሎውን ጭኖ ኮቱን ለበሰ፡፡
ይህንን ባየ ጊዜ ናስረዲን “እኔ በጣም አርጅቻለሁ፣ በእግሬ መጓዝ አልችልም፡፡ በጣም ስለበረደኝም ወደ ዳኛ እንድሄድ ከፈለክ ኮትህን ለብሼ በቅሎህን መሳፈር አለብኝ፡፡” አለው፡፡
ስስታሙም ሰው 1000 ፓውንዱን ማጣት ስላልፈለገ በሃሳቡ ተስማማ፡፡
ከዚያም ጉዟቸውን ወደ ፍርድ ቤት ቀጠሉ፡፡ ናስረዲንም ዳኛውን በርቀት ባየው ጊዜ ኮት ለብሶ በቅሎዋን የተሳፈረው እሱ መሆኑን ዳኛው እንዲያይለት መጮህ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ቃዲው ድምፁን ሰምቶ ሲመለከት ሽማግሌውን ሰው ከበቅሎው ላይ አየው፡፡ ናስረዲን ከበቅሎዋ ላይ ወርዶ ካሰራት በኋላ ከሳሽና ተከሳሽ ከዳኛው ፊት ቀረቡ፡፡
ከሣሹ ስስታም ሰው “ጌታዬ ይህ ሽማግሌ አምላክን ‘1000 ፓውንድ ስጠኝ፡፡ ከዚያ ያነሰም ሆነ የበለጠ አልቀበልም’ ብሎ ሲፀልይ ሰምቼ ልፈትነው በማሰብ 999 ፓውንድ ብሰጠው ቃሉን አጥፎ ገንዘቡን ወስዷል፡፡” ብሎ ከሰሰው፡፡
ናስረዲንም በተራው “ጌታዬ ይህ ሰው እብድ ነው፡፡ ይህንን ማረጋገጥ እችላለሁ፡፡ በእርስዎ ፊት ይህንን የለበስኩትን ኮት የእኔ ነው ይላል፡፡” አለ፡፡
ስስታሙም ሰው አቋርጦት “በእርግጥ ኮቱ የኔ ነው!” ብሎ ጮኸ፡፡ ናስረዲንም በመቀጠል “በኮቱ ብቻ አይደለም የማረጋግጠው፡፡ በበቅሎ ስመጣ እርስዎ ጌታዬ አይተዋል፡፡ እሱ ግን በቅሎው የኔ ነው ይላል፡፡” አለ፡፡
ስስታሙም ሰው በድጋሚ “በእርግጥም የእኔ ነው::” ብሎ ጮኸ፡፡ ቃዲውም እውነትም ስስታሙ ሰው እብድ ነው ብሎ በማሰብ አባረረው፡፡ ወደ የቤታቸው ሲመለሱ ስስታሙ ሰው እጅግ በጣም አዝኖ ነበር፡፡
ናስረዲንም ጠርቶት “በሰውና በአምላክ መሃከል ለምን ለመግባት ትሞክራለህ? ሁለተኛ ይህ ድርጊት እንዳይለምድህ፡፡” ብሎ ገንዘቡን መለሰለት፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|