ሼክ ናስረዲን በመንታ መንገድ ላይ
በሃጂ አብዱሰታር መሃመድ በሽር የተተረከ
አንድ ቀን ናስረዲን ወደጫካ ሄዶ ከአንድ ዛፍ ላይ በመውጣት የተቀመጠበትን ቅርንጫፍ መቁረጥ ጀመረ፡፡
ታዲያ በስፍራው የነበረ አንድ ወጣት ናስረዲንን “አንተ ሽማግሌ፣ ምን እያደረክ ነው? የተቀመጥክበትን ቅርንጫፍ ለምንድነው የምትቆርጠው? ትወድቃለህ እኮ” አለው፡፡
ናስረዲንም “አልወድቅም፡፡” ብሎ መቁረጡን ቀጠለ፡፡
በዚህን ጊዜ ቅርንጫፉ ተቆርጦ ሲወድቅ ናስረዲንም አብሮ ወደቀ፡፡ ከወደቀበትም ተነስቶ ወጣቱን ልጅ ፍለጋ ሄደ፡፡ ልጁንም ሲያገኘው የሚሞትበትን ቀን ጠየቀው፡፡
ወጣቱም ልጅ “የምትሞትበትን ቀን እንዴት ልነግርህ እችላለሁ?” አለው፡፡
ናስረዲንም “ከዛፉ ላይ ልወድቅ እንደምችል ነግረኸኛልና የምሞትበትንም ቀን ልትነግረኝ ይገባል፡፡” አለው፡፡
ሆኖም ወጣቱ ልጅ የነገረው ነገር ግልፅና የሚታይ እንደሆነ ሊያስረዳው ቢሞክርም ናስረዲን አሻፈረኝ አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ወጣቱ “እንግዲያው ወደ ቤትህ ስትመለስ በመንገድህ ላይ አንድ መንታ መንገድ ታገኛልህ፡፡ እዚያም ስትደርስ አንድ አህያ ሲያናፋ ትሰማለህ፡፡ በዚያን ጊዜ የህይወትህ ግማሽ አካል ይሞታል፡፡ አህያው ለሁለተኛ ጊዜ ሲያናፋም ሙሉ ለሙሉ ሞተህ ነፍስህ ከስጋህ ትለያለች፡፡” አለው፡፡
ከዚያም ናስረዲን ወደ ቤቱ መመለስ ጀመረ፡፡ መንታ መንገዱም ላይ እንደደረሰ አንድ አህያ ሲያናፋ በሰማ ጊዜ የህይወቱ ግማሽ እንደሞተ አሰበ፡፡ ከትንሽ ቆይታም በኋላ አህያው ደግሞ አናፋ፡፡ በዚህም ጊዜ ናስረዲን መሞቱን አምኖ ከመንገዱ ዳር ላይ ተጋደመ፡፡ በአጠገቡ ሲያልፉ የነበሩ ሰዎችም ባዩት ጊዜ ሊቀሰቅሱት ቢሞክሩም አልቻሉም፡፡
በዚህን ጊዜ “ይህ ሽማግሌ ሞቷል፡” አሉ፡፡
ከዚያም ዛፍ ቆርጠው አልጋ በመስራት ተሸክመውት ሄዱ፡፡ ለረጅም ጊዜ ከተጓዙም በኋላ ሌላ መንታ መንገድ ላይ ደረሱ፡፡ አንዳንዶቹ “ይህ ነው አጭሩ መንገድ” ሲሉ ሌሎቹ “አዎ አቋራጭም ነው፣ ነገር ግን ብዙ ዳገትና ቁልቁለት አለው ስለዚህ በረጅሙና በተስተካከለው መንገድ እንሂድ፡፡” እያሉ ተከራከሩ፡፡
ናስረዲንም ክርክራቸውን በሰማ ጊዜ “አዳምጡኝ፣ በዚህ ዓለም ላይ በነበርኩ ጊዜ….” ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ሰዎቹ ደንግጠው መንፈስ ነው ብለው ወደ መሬት ለቀቁት፤ እርሱም የሆነውን ሁሉ በነገራቸው ጊዜ ሁሉም ስቀውበት ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|