ሼክ ናስረዲን በዝናብ ውስጥ
በሃጂ አብዱሰታር መሃመድ በሽር የተተረከ
አንድ ቀን ሼክ ናስረዲን ከቤቱ መስኮት አጠገብ ተቀምጦ ሳለ አንድ ጎረቤቱ የሆነ ሰው በከባድ ዝናብ ውስጥ ሲሮጥ አየው፡፡ ሰውየውንም በመጣራት “ይህ ዝናብ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ለምንድነው የምትሸሸው?” አለው፡፡ ጎረቤቱም ሰው ምን ብሎ መመለስ እንዳለበት ስላላወቀ በድርጊቱ አፍሮ ቀስ ብሎ መራመድ ስለጀመረ ዝናቡ አበሰበሰው፡፡
(ተራኪው ለሌላ ሰው የተትረፈረፈ የእህል ክምር ከሰጠህ ለአንተም የተትረፈረፈ እህል ይከመርልሃል የሚል ትርጉም ያለው ተረትና ምሳሌ ተናገረ፡፡)
ከዚያ በኋላ ታዲያ አንድ ቀን ጂሃ ናስረዲን (ጂሃ የናስረዲን ተጨማሪ ስሙ ነው) በመንገድ ላይ እየሄደ ከባድ ዝናብ በመጣ ጊዜ የጎረቤቱ ሰው ከቤቱ መስኮት አጠገብ ተቀምጦ ናስረዲን ሲሮጥ አየው፡፡ እሱም በተራው ተጣርቶ “የአምላክ ስጦታ ከሆነው ዝናብ ለምንድነው የምትሸሸው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ናስረዲንም “አየህ፣ እኔ የምሮጠው የአምላክ ስጦታ ላይ ቆሜ እንዳላቆሽሸው ስለፈለኩ ነው፡፡” ብሎት ብዙ ሳይበሰብስ ወደቤቱ ሮጦ ገባ ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|