የሃይቁ ዳርቻ እሳት
በሃጂ አብዱሰታር መሀመድ በሽር የተተረከ
የአቡ ናዋስ እውነተኛው ስሙ ሃሰን ቢን ሃኒ ነው፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖር ሃብታም ሰው አንዲት በጣም ቆንጆ ልጅ ነበረችው፡፡
እሱም “ልጄን ማግባት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው አንድ ሌሊት ሙሉ በሃይቁ ውስጥና ከዚያም በጣም ቀዝቃዛ ውሃ ወደ ከበበው ደሴት በመዋኘት ወጥቶ ከዚያ በኋላ እንደገና በዋና ወደ ሃይቁ ዳርቻ መውጣት አለበት፡፡” አለ፡፡
ታዲያ አንድ ከእናቱ ጋር አብሮ የሚኖር ወጣት ይህንን ለማድረግ በመወሰን የሃብታሙን ሰው ልጅ ለማግባት መሞከር ፈለገ፡፡
ስለዚህ በሃይቁ አድርጎ ወደ ደሴቱ በመዋኘት እዚያ አንድ ሌሊት አሳለፈ፡፡ እናቱም ሃይቁ ዳርቻ ላይ እሳት በማቀጣጠል የልጇን መመለስ መጠባበቅ ጀመረች፡፡ ይሞታል ብላም ፈርታ ነበር፡፡
ሲነጋጋ ወጣቱ ልጅ በዋና ከሃይቁ በመውጣት ወደ ሃብታሙ ሰው ቤት ሄዶ ሌሊቱን በደሴቱ ላይ ከአንድ አለት ላይ ማሳለፉን ነግሮት ልጁን በሚስትነት እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡
ሃብታሙ ሰው ግን “እናትህ እሳት ይዛ ስለጠበቀችህ ልጄን አልሰጥህም፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ወጣቱ ልጅ ወደ ቃዲ (የእስልምና ዳኛ) ዘንድ ሄደ፡፡
ቃዲውም “እናትህ እሳት ይዛ ስለጠበቀችህ የእርሱን ልጅ ማግባት አትችልም፡፡” አለው፡፡
ወጣቱ ልጅ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገባው፡፡ ግራ ተጋብቶ ሳለ አቡ ናዋስን አግኝቶ ስለሁሉም ነገር አጫወተው፡፡
አቡ ናዋስም “አይዞህ፣ ችግርህን ለመፍታት እኔ እረዳሃለሁ፡፡” አለው፡፡ አቡ ናዋስ ቃዲውንና የወጣቱን ልጅ ቤተሰብ ከከተማው ዳርቻ ላይ በሚገኝ አንድ የእርሻ ቦታ ላይ ድግስ አዘጋጅቶ ጠራቸው፡፡
አንድ ኮርማ በሬም አርዶ ስጋውን መጥበሻ ላይ በማስቀመጥ መጥበሻውን ዛፍ ላይ በመስቀል ከመጥበሻው ስር እሳት አቀጣጠለ፡፡ ሰዎቹ ስጋውን ስላዩ ምሳ ለመብላት በጣም ፈልገው ነበር፡፡ ትዕግስታቸውም ስላለቀ “ምንድነው የምንበላው?” ብለው ጠየቁት፡፡
እርሱም “ታገሱ፣ ገና አልደረሰም፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም “መጥበሻውን ከእሳቱ አርቀህ ዛፍ ላይ ሰቅለኸው እንዴት ታገሱ ትለናለህ? ስጋው እንዴት ሊበስል ይችላል?” አሉት፡፡
እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰ “ይህ ወጣት ልጅ አንድ ሌሊት በቀዝቃዛው የሃይቅ ዳርቻ አሳልፏል፡፡ ነገር ግን እሳቱን እያየ እንዴት ሊሞቀው ይችላል? ከዚያ እሳትም ሙቀት ሊያገኝ እንደማይችል እያወቅህ ልጅቷን እንዴት አታገባም ትለዋለህ?”
ከዚያም ቃዲው “ትክክል ነህ፣ የጠየከውንም እንቀበላለን፡፡ ሃብታሙ ሰውም ጥያቄውን ይቀበላል፡፡” አለው፡፡
ከዚያ በኋላ መጥበሻውን አውርደው ስጋውን በማብሰል ተመገቡ፡፡ በመጨረሻ ሁለቱ ወጣቶች ተጋቡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አቡ ናዋስ የወጣቱን ልጅ ጉዳይ እንዲህ አድርጎ ረታ ተብሎ ይነገራል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|