ጥሩዋ ሚስት
በዩሱፍ አማን ኦስማን የተተረከ
ይህ የሆነው በአሚሮቹ ዘመን ሲሆን የአሚሩ የበኩር ልጅ ለአካለ መጠን በደረሰ ጊዜ ችግር መፍጠር ጀመረ፡፡ በጣም ጠበኛና በጥባጭም ሆነ፡፡ አሚሩ ምን እንደሚያደርግ ግራ ገባው፡፡
ከዚያም የአሚሩ የቅርብ ጓደኛ ወደ አሚሩ ዘንድ ሄዶ “አዳምጠኝ፣ አንድ ልጅ ወደ ወጣትነት ሲያድግ ስሜቶቹን በተለያየ ውስብስብ ሁኔታዎች ነው የሚገልፀው፡፡ እናም ምናልባት ይህ ልጅ ልጃገረድ አግኝቶ ማግባት ፈልጎ ወይም ሌላ ነገር ፈልጎ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለብልህ ሴት ብትድረው በረድ ሊል ይችላል፡፡ እናም የሚያስቸግርህ ማግባት ስለፈለገ ነውና ዳረው፡፡” ብሎ ይመክረዋል፡፡
አሚሩም በዚህ ተስማምቶ በከተማው ውስጥ በጣም ምርጥ ልጃገረድ ካፈላለገ በኋላ አንዲት ልጅ አግኝቶ ልጁም ከሚስቱ ጋር አብሮ መኖር ጀመረ፡፡
ሆኖም ስለእሷ ጥርጣሬ ይገባው ስለጀመረ በየደቂቃው ይጨቀጭቃትና “ከሌላ ሰው ጋር ፍቅር ጀምረሻል::” በሚል ይኮንናት ጀመር፡፡ ወጣቱ ልጅም እሱ ከቤት በወጣ ጊዜ እቤት ማን መጥቶ እንደነበር ይጠይቅ ጀመር፡፡
“እዚህ ሲጋራ ሲያጨስ የነበረው ማነው? ከቢሮ ስደውልልሽ ከማን ጋር ነበርሽ? ድምፅ ይሰማኝ ነበር፡፡” እያለ ይነዘንዛት ጀመር፡፡
ልጅቷም በጣም መጨነቅ ስለጀመረች ምን እንደምታደርግ ግራ ገባት፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ነገሮች ተባብሰው ይደበድባት ጀመር፡፡ እሷም ወደራሷ ወላጆች ሳይሆን ወደእርሱ ወላጆች ሸሽታ ሄደች፡፡ እየሮጠች ከቤት በገባችም ጊዜ አሚሩ “ምን ሆነሽ ነው?” ብሎ ጠየቃት፡፡
እሷም “ልጅህ አብዷል፤ምን እንደማደርግ አላውቅም፡፡” አለችው፡፡ ልጁም ወደቤት ሲመጣ በልጁ የተበሳጨው አሚር ልጁን በጥፊ ከመታው በኋላ እጅና እግሮቹን አስሮ ከአንድ ጥግ አስቀመጠው፡፡ ሚስቱም “ከዚህ የትም አልሄድም እዚህ አብሬአችሁ እየኖርኩ እኔው እራሴ እመግበዋለሁ፡፡” አለች፡፡
ምግቡንም እርሱ ፊት ታበስልለት ጀመር፡፡ ተረጋግቶ እንደሆነም ትጠይቀዋለች፡፡ መልስ ሳይሰጣት ሲቀር ከዚህ የባሰ እንደምታሰቃየው ትነግረዋለች፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ሰገራው ያለበትን ፖፖ ወደ አንድ ጎን አስቀምጣ ምግቡን ከእርሱ ፊት ስታበስል ከሰገራው ላይ አንድ ማንኪያ በመውሰድ ምግቡ ላይ ጨምራ “ገና ብድሬን እመልሳለሁ፡፡” አለችው፡፡
ምግቡንም ስትሰጠው በቁጣ ጮኸባት፡፡
አሚሩም ጩኸቱን ሰምቶ ወደ ክፍሉ መጥቶ ሲገባ “ተመልከት፣ አሁንም አልወጣለትም፡፡ ተመልከት” አለችው፡፡
አሚሩ በጣም ስለተበሳጨ በዱላ እየደበደበው ምግቡን እንዲበላ አደረገው፡፡
ከዚያም አሚሩ “ይህ ጥሩ ምግብ ነው፡፡ እንዴት ብትደፍር ነው ሰገራ አለበት የምትለው?” አለው፡፡
በመጨረሻ ከዚህ ስቃይ መላቀቂያው ብቸኛ መንገድ ሚስቱን ይቅርታ መጠየቅ መሆኑን ተረድቶ በመምበርከክ ይቅርታዋን ሲጠይቃት እሷም ይቅር ስላለችው ከእስሩ ተፈትቶ በደስታ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|