ጅብና ቀበሮ
በዘይነባ አቢበከር ደረሞ የተተረከ
ከዕለታት አንድ ቀን ጅብና ቀበሮ ቤት ፍለጋ ይሄዳሉ፡፡ ጅቡ ትልቅ ቤት ሲያገኝ ቀበሮዋ ብዙ ቀዳዳዎች ያሉት ትንሽ ቤት አገኘች፡፡ ቀበሮዋም ጅቡን “አንበሳ ቢመጣብህ በየት በኩል ታመልጣለህ? እኔ ግን በቀዳዳዎቹ አመልጣለሁ፡፡” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ጅቡ ቤት እንድትቀይረው ለምኗት ቤታቸውን ተቀያየሩ፡፡
ቀበሮዋም ቤቷን ቆልፋ ውስጥ ተቀመጠች፡፡ አንበሳም በመጣ ጊዜ ጅቡ አንበሳውን አባረረው፡፡
ከዚያ ጅቡና ቀበሮዋ እንደገና ተገናኝተው ምግብ እንፈልግ በማለት ምግብ ፍለጋ ተሰማሩ፡፡ ጅቡ ወፍራም በሬ ሲያገኝ ቀበሮዋ ተባይ የሞላበት አህያ አገኘች፡፡
በዚህ ጊዜ ቀበሮዋ ጅቡን “ተመልከት የእኔ አህያ ብዙ ጮማ ስላለው እያንጠባጠበ ነው የሚሄደው፤ ያንተ ግን ምንም የሚያንጠባጥበው ቅባት የለውምና እንቀያየር” አለችው፡፡
ተቀያየሩም፡፡
ከዚያ በኋላ እንደገና ሲገናኙ ቢላዋ ፍለጋ ተሰማሩ፡፡ ጅቡ ቢላዋ ሲያገኝ ቀበሮዋ ግን ላባ አገኘች፡፡
ቀበሮዋም እንዲህ አለች “አንተ ቢላዋ አለህ፡፡ ነገር ግን ቢሰበርብህ ምንም ማረድ አትችልም፡፡ እኔ ግን በቀላሉ ሌላ ላባ ስለማገኝ እንቀያየር” ብላው ተቀያየሩ፡፡
ከዚያ ቀበሮዋ በቢላው በሬውን ስታርድ ጅቡ ግን አልቻለም፡፡
“አህያውን በዚህ ላባ ላርደው አልችልም፡፡ አንቺ ልታርጂው ትችያለሽ?” ብሎ ጅቡ ቀበሮዋን ጠየቃት፡፡
ቀበሮዋም ቢላውን ጅቡ እንዳያየው በላባው ሸፍና አህያውን በማረድ አብረው በሉ፡፡
ከዚያም ሄደው መንገድ ላይ ተቀምጠው ሳለ ማርና ቅቤ የተሸከመ ግመል አዩ፡፡
ቀበሮዋም ከግመሉ ጋር የሚጓዙትን ሰዎች “ደክሞኛል፤ እባካችሁ ግመሉ ላይ ጫኑኝ::” ብላ ለመነቻቸው፡፡
እነርሱም ጭነዋት ሲሄዱ ቀበሮዋ ማሩንና ቅቤውን ሙልጭ አድርጋ በልታ ቅሎቹን በሽንቷ ሞላቻቸው፡፡
ከዚያም “ቤቴ ደርሻለሁና እዚህ አውርዱኝ፡፡” አለቻቸውና ወረደች፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ገበያ ሄደው ማሩንና ቅቤውን ለመሸጥ ቅሎቹን አውርደው ሲከፍቷቸው መጥፎ ጠረን ሸተታቸው፡፡
ገዢውም “ይህ ምንድነው? ይገማል፡፡” አላቸው፡፡
የግመሉ ባለቤቶችም “አንዲት ቀበሮ ደክሞኛል ብላ ስትለምነን ጭነናት እቤቷ ስትደርስ አውርደናት ነበር፡፡” አሉት፡፡
ከዚያ በኋላ ቀበሮዎችን ሁሉ አንድም ሳይቀር ሰብስበው እንዲዘሉ በማድረግ ማርና ቅቤያቸውን የበላችው ግን ስለሚከብዳትና መዝለል ስለማትችል በዚህ ሊለዩዋት ወሰኑ፡፡ ከዚያም ከአጥፊዋ ቀበሮ በስተቀር ሁሉም ያለምንም ችግር ስለዘለሉ ሌባዋን ቀበሮ በመያዝ አስረዋት በኋላ ሊገርፏት ትተዋት ሄዱ፡፡
ከዚያም ጅቡ መጥቶ “ምን ሆነሻል? ለምንድነው የታሰርሺው?” አላት፡፡
ቀበሮዋም “ቅቤና ማር መብላት አልፈልግም ስላቸው አስረውኝ ሄዱ፡፡” አለችው፡፡ ጅቡም “ልፍታሽና እኔን እሰሪኝ፡፡” አላት፡፡
ነጋዴዎቹም ተመልሰው ሲመጡ ጅቡን ይገርፉት ጀመር፡፡
እሱም “ተውኝ፣ ተውኝ” ሲላቸው፡፡
“እዚህ ምን ትሰራለህ?” አሉት፡፡
“ቀበሮዋ ቅቤና ማር ታገኛለህ ስትለኝ እኔን እንድታስረኝ ጠይቄአት ነው፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ቀበሮዋ ዛፍ አናት ላይ ወጥታ በኦሮምኛ “አይኑን አትግረፉት፣ ጆሮውን አትግረፉት፣ ነገር ግን ሌላ ቦታ ግረፉት፡፡” አለቻቸው፡፡
ሰዎቹም ጅቡን ሲገርፉት ስጋው ከላዩ ላይ ስለተነሳ ለቀውት ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤት እንደደረሰም ልጆቹ አይተው “አሃ! አባታችን ስጋ አመጣልን፡፡” ብለው በሉት፡፡
የጅብ ሞኝነት ህይወቱን አሳጣው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|