አንበሣና ጦጣ
በራምሴ ሽዎል የተተረከ
በድሮ ጊዜ ሁሉም እንስሳት አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ሁሉም አብረው ሲኖሩ የየራሳቸውን ጉዳይ የሚመለከት አለቃ ነበራቸው፡፡
ታዲያ በዚያን ጊዜ አንድ ጦጣ ከአንበሳ ተበድሮ ስለነበር አንበሳው ሁልጊዜ ገንዘቡን እንዲመልስለት ጦጣውን ይጠይቀው ነበር፡፡
ሁልጊዜም “ገንዘብህን እሰጥሃለሁ::” ይለዋል እንጂ ሰጥቶት አያውቅም፡፡
ጦጣውም አንበሳውን ባየው ቁጥር አንበሳው እንዳይዘው ይደበቅ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን አንበሳው ወደ አለቃው ሄደ፡፡ አለቃውም ቀበሮ ነበርና አንበሳው ጦጣውን ለቀበሮው ከሰሰው፡፡
“ቀበሮ ሆይ! እዳ አለኝ፡፡ ገንዘቤ በጦጣ ተወስዶ ጦጣው እስካሁን ሊከፍለኝ ስላልቻለ ከዚህም በኋላ የሚመልስልኝ ስለማይመስለኝ እባክህ ጉዳያችንን ተመልከት፡፡” አለው፡፡
እናም ሁሉም እንስሳት ተጠሩ፡፡ ላም፣ በግ፣ፍየል ፣አይጥ ፣ጅብ ጎሽና ሌሎችም ብዙ እንስሳት፡፡ ከዛፍም ስር ተሰብስበው በአንበሳውና በጦጣው መሃከል የተነሳውን ውዝግብ ማዳመጥ ጀመሩ፡፡
እናም ጉዳዩ በጥልቀት ከታየ በኋላ አለቃው ጦጣውን ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኘው ገንዘቡን ካልከፈለ በአንበሳው ከመበላት ያለፈ ሌላ አማራጭ እንዳልነበረው ተናገረ፡፡
አንበሳው በጣም ጠንካራ እንስሳ ስለሆነና ማንኛቸውም እንስሳት ሊያሸንፉት ስለማይችሉ ሁሉም ይፈሩታል፡፡ በዚህ ፍራቻ የተነሳ ጦጣው ተፈረደበት፡፡
“ገንዘቡን ካልከፈልክ መበላት አለብህ፡፡” ተባለ፡፡
መጀመሪያም ጦጣው በአንበሳው ይበላ ዘንድ ፍርዱን ያስተላለፈችው ላም ስትሆን ሁሉም እንስሳት በፍራቻ ተመሳሳይ ፍርድ ሰጡ፡፡
አለቃቸው ቀበሮም ጦጣው በአንበሳው እንዲበላ በሁሉም እንስሳት እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ ይህንን ሃሳብ አልወደደውም፡፡ አንበሳው ጦጣውን ይብላው የሚለው ሃሳብ አልተዋጠለትም፡፡
በመጨረሻም እንግዲያው “አያ ጦጣ ሆይ በአንበሳው እንድትበላ ተፈርዶብሃል፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው ከመበላቱ በፊት ዛፉንም ማየት ይችላል፡፡ ዛፉን ማየት ትችላለህ፡፡ ዛፉም ከኋላህ ነው ያለው፡፡ እኔም ብሆን እንደሌሎቹ እንስሳት ሞት ፈርጀብሃለሁ፡፡ እናም ፍርዱ በሙሉ ድምፅ እንድትበላ የተላለፈ ነው፡፡ ነገር ግን ዛፉን እያየህ መበላት ትችላለህ፡፡” አለ አለቃቸው ቀበሮ፡፡
በዚህ ጊዜ ጦጣው ቀበሮው ማለት የፈለገው ነገር ስለገባው በፍጥነት ዘሎ ዛፍ ላይ ሲወጣ ሁሉም እንስሳት ተበታትነው አንበሳውም ጦጣውን እንዳይበላው ጦጣው በዛፉ ራሱን አዳነ፡፡
ይህ ህጻናትን የሚያስተምረው ከሌላ ሰው የተዋሳችሁትን ንብረት መልሳችሁ መክፈል እንዳለባችሁ ነው፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ ቀበሮው እንደአለቃነቱ ከጠንካራው ሣይሆን ከደካማው መወገኑንና ድምፅ አሰጣጡ ግን ዲሞከራሲያዊ የሆነና በሁሉም እንስሳት የተወሰነው ጦጣው እንዲበላ ነበር፡፡ ነገር ግን ለጊዜው ቢያመልጥም ህይወቱን በሽሽት ይኖራል፡፡ ይህ ለእርሱ በቂ ቅጣት ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|