አምላክና ሰው
በራምሴ ሽዎል የተተረከ
ከስነ ፍጥረት ጀምሮ ፈጣሪ ለሰዎች ቅርብ ነበር፡፡ ሁልጊዜም ያነጋግራቸው ነበር፡፡ በጣም ብዙ አይነት ሰዎች ብዙ የተለያዩ ሃሳብ ያላቸውና የተለያዩ ምኞት ያላቸው ሰዎች ሁልጊዜ ያጉረመረሙ ነበር፡፡
ብዙውን ጊዜ ፀሃይ ስትወጣ አንዱ ሰው “አምላክ ሆይ እባክህ የጠዋቱ እንቅልፍ በጣም ጣፋጭ ስለሆነ ጸሃይዋ አሁን ሳይሆን ትንሽ ቆይታ ትውጣ፡፡” ይላል፡፡
አምላክም “እውነትህን ነው፡፡ እንግዲያው ትንሽ አቆያታለሁ፡፡” ይላል፡፡ በሌላ በኩል ፀሃይዋን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የፈለጋት ሰው ደግሞ “እባክህ ለምንድነው ፀሃይዋን ያዘገየሀት? ፀሃይዋ ለምንድነው የማትወጣው?” ይላል፡፡
ከዚያም ፈጣሪ ፀሃይዋን ያወጣታል፡፡
በቀን ደግሞ በሞቃት ፀሃይ ውስጥ የሚሄድ ሰው “አምላኬ ሆይ እባክህ በሙቀቱ ምክንያት በጣም ስለደከመኝና ፀሃይዋም በጣም ስለምታቃጥል ትጥለቅ” ይላል፡፡
አምላክም ወዲያው ፀሀይዋ እንድትጠልቅ ያደርጋል፡፡
ሌላኛው ሰው ደግሞ ወደ ሩቅ ቦታ እየተጓዘ ሳለ ከሥፍራው ከመድረሱ በፊት እሱም “አምላኬ ሆይ ፀሀይዋ ለምን እንድትጠልቅ አደረክ? ከምሄድበት ሥፍራ እስክደርስ ድረስ ትንሽ ከፍ አድርጋት፡፡” እያለ ያላዝናል፡፡
ፀሃይዋም ያ ሰው ካሰበው ሥፍራ እስኪደርስ ትንሽ ከፍ ብላ ትቆያለች፡፡
በዚህ ሁኔታ ማንገራገሩ በጣም ስለበዛ አምላክ በጣም ተቸገረ፡፡ አንዱ አንድ ነገር ሲል አምላክ ይሰማዋል፤ ሌላው ሌላ ነገር ሲል አምላክ ይሰማዋል፡፡ ስለዚህ ከብዙ ሰዎች በሚመጣ የተለያየ ጥያቄ ፈጣሪ ግራ ገባው፡፡
በዚህ ጊዜ ብልጡ ቀበሮ “ፈጣሪ ሆይ ለሰዎች ቅርብ እስከሆንክ ድረስ ሁልጊዜም ስለምታዳምጣቸው ሁሌም ትረበሻለህ፡፡ ከሰዎች ራቅ፡፡ አትስማቸውም፡፡ ሁልጊዜም በተዘዋዋሪ መንገድ ስጣቸው፡፡ አንተ የሰው ፍጡር አይደለህም፡፡ አንተ በሥፍራህ አምላክ ነህና የእነዚህን ሰዎች ልዩ ልዩ ችግሮች አትስማ፡፡ ከእኛ ርቀህ ሂድና በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ብቻ ባርከን፡፡ ፍጥረታትህ የአንተ ፍጥረታት ስለሆኑ አንተ መረበሽ የለብህም፡፡” አለው፡፡
ከዚህም በኋላ ፀሃይ በነበረችበት ቀጠለች፤እየወጣችና እየገባች፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|