የቀበሮው ታሪክ
በጆን ኩራንግ የተተረከ
አንድ ቀበሮ ሜዳው እንዲስተካከልለት ፈልጎ ሜዳውን የሚያፀዱለት ሰዎች ማሰባሰብ ጀመረ፡፡ በጠዋት ተነስቶም ወደ ውሻ ሄደ፡፡
“ነገ ጠዋት በመስኬ ላይ ስራ ይከናወናል፡፡” አለው፡፡
ውሻውም “ጠላቴ ነብርን ጠይቀኸዋል? መጥቶ አይገድለኝም?” ብሎ ጠየቀው፡፡
“አይ እሱን አልጋበዝኩትም፡፡ እኔና አንተ ብቻ ነን፡፡” አለው፡፡ ውሻውም በዚህ ተስማማ፡፡ ከዚያም ቀበሮው ወደ ነብሩ ሄዶ ነገ “በእኔ መስክ ላይ ስራ እንሰራለን፡፡” አለው፡፡
“እሺ” አለ ነብሩ “መጥቼ እረዳሃለሁ፡፡”
ቀጥሎም ቀበሮው በጉን አነጋገረው፡፡
“ነገ እኔ መስክ ላይ ስራ ስላለ መጥተህ እርዳኝ፡፡” አለው፡፡
በጉም “ጠላቴ ጅብን እንዲመጣ ጋብዘኸዋል?” ብሎ ጠየቀው፡፡
“አይ አልጋበዝኩትም፣ እኔና አንተ ብቻ ነን::” አለው፡፡
ነገር ግን ከዚያ በኋላ ጅብ ጋ ሄዶ ጋበዘው፡፡
“ነገ እኔ መስክ ላይ ስራ ስለምሰራ መጥተህ እርዳኝ፡፡” አለው፡፡ ጅቡም ተስማማ “እሺ እመጣለሁ፡፡” በማለት፡፡
ቀጥሎ ቀበሮው ዶሮ ዘንድ በመሄድ “ነገ እኔ መስክ ላይ ስራ አንሰራለን፡፡” አላት፡፡
ዶሮዋም “እኔ እኮ ብዙ ጠላቶች አሉኝ እነርሱንም ጠርተሃል?” አለችው፡፡
ቀበሮውም “አይ እኔና አንቺ ብቻ ነን፡፡” አለ፡፡ እናም ዶሮዋ “እሺ” አለች፡፡
ከዚያም ቀበሮው ወደ ዶሮዋ ጠላቶች በመሄድ “ነገ እኔ መስክ ላይ ስራ ስለምንሰራ ልትረዱኝ ትችላላችሁ?” አላቸው፡፡ እነርሱም “እሺ እንመጣለን፡፡” አሉት፡፡
ሁሉም ሠራተኞች ታዲያ “አንተ መስክ ላይ ስንሰራ ውለን ምንድነው የምንበላው?” ብለው ጠየቁት፡፡
ቀበሮውም “ሃሳብ አይግባችሁ፡፡ በጣም ጥሩ ወይን አዘጋጃለሁ፡፡” አላቸው፡፡
እናም ሁሉም እንስሳት መኮትኮቻውን ይዘው ወደ ቀበሮው ማሳ መጡ፡፡ መጀመሪያ የተጠራው ውሻ ቀድሞ መጣ፡፡
ከዚያም ነብር ሲመጣ ገድሎ ሊበላው የሚፈልገውን ውሻ አየ፡፡ በጓም ጅቡን ስታይ ፈራች፡፡ ውሻውና ዶሮዋም ፈርተው ነበር፡፡
ከዚያም ሥራውን ጀምረው እስከ ስምንት ሰአት ከስሩ በኋላ “ትናንት ቃል የተገባልን ወይን የታለ? አሁን መጠጣት እንፈልጋለን፡፡” እያሉ አጉረመረሙ፡፡
ቀበሮውም “ትንሽ ታገሱኝ፡፡ ሁሉንም ነገር እያዘጋጀሁ ነው፡፡” አለ፡፡ አሁንም ሥራቸውን ቀጥለው እስከ ዘጠኝ ሰአት ከሰሩ በኋላ ሁሉም ስለደከማቸው ቁጭ አሉ፡፡
ቀበሮውንም “ለምንድነው የምታስጠብቀን? ተመልከት ደክሞናል እኮ፡፡ ወይኑን አምጥተህ ለምንድነው የማትሰጠን?” አሉት፡፡
በዚህ ጊዜ ቀበሮው “እሁንስ ውትወታችሁ ሰለቸኝ፡፡ እያንዳንዳችሁ የምትችሉትን ነገር ሄዳችሁ ብሉ፡፡” አላቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ሃያላት እንስሳት ሰለባዎቻቸውን እያሳደዱ በመግደል ሲበሉ አካባቢው ድብልቅልቁ ወጣ፡፡
ይህ ታሪክ የቀበሮው ማሳ የሚባለውን ተረትና ምሳሌ የሚያሳይ ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|